በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገበው ስኬትና የተገኘው ውጤት አበረታች ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገበው ስኬትና የተገኘው ውጤት አበረታች ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገበው ስኬትና የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት የ2018 በጀት ዓመት የመንግስትና የፓርቲ ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ የትውውቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገበው ስኬትና የተገኘው ውጤት አበረታች ነው።
እንደ ሀገር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በመሰረተ ልማት ግንባታና በማህበራዊ ሴክተሮች ጭምር የሚጨበጥ ውጤት መጥቷል ብለዋል።
የክልሉን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ ረገድም በቅንጅትና በትብብር በመስራት ህግን በማስከበርና የልማት ስራዎችን በማጠናከር የተመዘገበውን ስኬትም ለአብነት አንስተዋል።
እንዲሁም ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውን ፅንፈኛ ቡድን እና የፖለቲካ ፅንፈኝነትን በተደራጀ አግባብ አምርሮ በመታገል አስተሳሰቡን በማክሸፍ አበረታች ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በክልሉ የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ባለፈም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ኢኮኖሚያዊ መሳለጥን የሚያግዙ መሰረተ ልማትን በመዘርጋት፣ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት እና የስራ እድል በመፍጠርም አበረታች ስራ እንደተሰራ አረጋግጠዋል።
መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመታገል፣ ውስጣዊ የገቢ አቅምን በማሳደግ በኩልም የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሰላምን ከማጽናት ጎን ለጎን የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ውጤቶች የበለጠ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ነገር ግን አሁንም ያልተፈቱና ያደሩ የፀጥታ ችግሮችን በተሻለ ቅንጅት መፍታት ይገባል ብለዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመት የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የገቢ መሰረትን በማስፋት፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በላቀ ቁርጠኝነት አመራሩ ምስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በመድረክ የጋራ መግባባትና ግንዛቤ በመፍጠር የመንግስትና የፓርቲ ስራዎችን በውጤታማነት መምራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
''አርቆ ማየት አልቆ መስራት'' በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው መድረክ ከነሐሴ 23 እስከ 27/2018 ዓ/ም የሚቆይ ሲሆን በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛል።