ቀጥታ፡

በአፍሪካ የወረርሽኝ ዝግጁነትና የምላሽ አቅም ግንባታ ላይ ያለውን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ ነን - የዓለም ባንክ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የዓለም ባንክ በአፍሪካ የወረርሽኝ ዝግጁነትና የምላሽ አቅም ግንባታ ላይ ያለውን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት የተካሄደው 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ የ76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ ሊቀመንበር ሆናም ተመርጣለች።

በጉባኤው ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያከናወነቻቸውን ስራዎች ተሞክሮ ያቀረበች ሲሆን የዘርፉን ተግዳሮቶች መፍታት የሚያስችሉ ውይይቶች እና ስምምነቶች ተደርገዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤና ስፔሻሊስት ጸጋነህ አምሳሉ 13 ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችላቸውን ስምምነት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህም በዋናነት ሀገራቱ መረጃዎችን፣ የመድሀኒት እና ሌሎች ነገሮች ለመለዋወጥ የሚያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ስምምነቱ በሽታዎች ከመከሰታቸው በፊት ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር ለሚደረገው ስራ መሰረት የሚጥል መሆኑን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ የስምምነቱ አካል መሆኗን ገልጸው፤ ስምምነቱ በሽታዎችን ከመከላከል ባለፈ የሀገራትን አቅም በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በሽታ የመከላከል እና የጤና መሰረተ ልማት ግንባታዎችን እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም በበሽታ መከላከል እንዲሁም በአቅም ግንባታ ላይ ለመደገፍ በስምምነቱ ቁርጠኛነቱን ማረጋገጡን አንስተዋል።

ባንኩ እነዚህን አቅሞች እየገነባ እንደሚቆይ ገልጸው፤ በቀጣይ በስምምነቱ ላይ የተቀመጡ ድርጊቶችን ሀገራት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ስምምነቱ በአህጉሪቱ የበሽታ ወረርሽኝ ዝግጁነትና ምላሽ ላይ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም