ለተሻለ ነገ መሰረት የጣለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
ለተሻለ ነገ መሰረት የጣለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር የኢትዮጵያን አንድነትና እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአርባ ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል።
በጉባኤው ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቁ የአለመግባባት ስብራቶችን በሐሳብ የበላይነትና በጥበብ መፍትሔ መስጠት እንደሚችሉ በተግባር አሳይተዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ምክክሩ ኢትዮጵያ ወደ አንድነትና የተሻለ ልማትና እድገት የምትሸጋገርበት ትልቅ ድል ነው።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሀምሳ አለቃ አብዱ ሁሴን እንደገለጹት፤ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎችን ያካተተ፤ ለሀገር የሚበጁ ጉዳዮች ላይ የተመካከሩበት ስኬታማ ሁነት ነው።
ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን ለመፍታት ችግሮችን በምክክር ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለማምጣት ያስቻለ መሆኑን ገልጸው፤ የአንድነት የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሃሊማ መሃመድ በበኩላቸው፤የሀሳብ ልዩነትን በኃይል ለመፍታት መመኮር ጊዜው ያለፈበት አካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምክክሩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፤በምክክር የምትገነባ ሀገር አሸናፊ ናት አሁን ኢትዮጵያ የአሸናፊነት ጉዞዋን ጀምራለች ብለዋል።
ምክክሩ ለትውልድ የሚበጅና ለሀገር አንድነት መሰረት የተጣለበት ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት ደግሞ አቶ አበበ ኮምቤ ናቸው።
ወይዘሮ ዘሪቱ አስቤ በበኩላቸው፤ቀደም ሲል በሀገሪቱ ችግሮችን ለመፍታት በጠረጴዛ ዙሪያ የመመካከር ልምድ እንዳልነበረ አንስተዋል።
ምክክሩ በችግሮች ላይ በመመካከርና በመፍታት ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።