ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አዲሱ የቱሪዝም ከፍታ!

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ከሀገሪቷ ልዩ ፀጋዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ሀገሪቱ ያሏት ጉምቱ ታሪክ፣ ብዝሃ ባህል እና ልዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለአፍሪካ ስልጣኔ ያላትን ታላቅ ድርሻ የሚያመላክቱ ናቸው።

ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንስቶ እስከ አክሱም ሀውልትና የጁገል ግንብ ድረስ ያሉት ቅርሶች የኢትዮጵያን የታሪክ ጥልቀት እና የባህል ትሩፋቶች በግልጽ ያሳያሉ።

እነዚህ ታሪካዊ ሀብቶች በአሁኑ ወቅትም የውጭ ጎብኚዎች፣ ተመራማሪዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቀልብ መሳባቸውን ቀጥለዋል። ከታሪክ ሀብቶቿ ባለፈም ማራኪው የመልክዓ ምድር አቀማመጥ፣ ብቅ ያሉ የዱር እንስሳቶች እና የዜጎች እንግዳ ተቀባይነት የአኗኗር ዘይቤ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

መንግስት ቱሪዝምን እንደ አንድ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶ በመውሰድ ስትራቴጂካዊ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተቀረጹት የ"ገበታ ለሸገር"፣ "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ከማውጣት ባለፈ የገቢ መጠንን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ለውጥ እያስመዘገቡ ነው።

ከዚህም መካከል በሶማሌ ክልል በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ዳርቻ ተገንብቶ በቅርቡ የተመረቀው እና የ"ገበታ ለትውልድ" አካል የሆነው የሸበሌ ሪዞርት አንዱ ማሳያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ሪዞርቱ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የገባነውን ቃል በተግባር ያረጋገጠ የምስራቁ የሀገራችን ክፍል ትልቅ ማሳያ ሥራ ነው።

ይህ ስራ በታችኛው የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ አካባቢ ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል የፈጠረና የክልሉን የቱሪዝም ገጽታ የቀየረ ነው።

በተጨማሪም በመዲናዋ አዲስ አበባ የተገነቡት የወዳጅነት አደባባይ፣ አንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም እና አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አዳዲስና ተመራጭ የከተማ ቱሪዝም (Urban Tourism) መዳረሻዎች ሆነዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዋና ከተማዋ የተከናወነው ሰፊው የኮሪደር ልማት ሥራ የአዲስ አበባን መልክ በአዲስ ሁኔታ በመግለጥ፣ ከተማዋን ለሰው ልጅ ምቹ፣ ውብ እና የጎብኚዎች ዓይን ይበልጥ የሚያርፍባት የቱሪስት ማዕከል አድርጓታል።

ከታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃ አንጻርም እድሳት የተደረገላቸው ብሔራዊ ቤተ መንግስት (ኢዮቤልዩ)፣ የጎንደር የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስታት፣ የጅማ አባጅፋር ቤተመንግስት እና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለዘርፉ መነቃቃት የጎላ አበርክቶ እያበረከቱ ይገኛሉ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ በቅርቡ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር እና የባልካሌ ውብ ተፈጥሮአዊ ጥንታዊ ቅርሶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ካርታ ይበልጥ አበልጽገውታል።

ይህ ዓለም አቀፋዊ እውቅና የሀገሪቱን የባህል እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጥረት ማሳደጉ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሚመጡ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ የቱሪዝም ገቢን ለማሳደግ አስችሏል።

በሌላ በኩል፣ የቱሪዝም ዘርፉን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ የአቪዬሽን እና የእንግዳ ተቀባይነት (Hospitality) አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ መሆናቸው ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መዳረሻ ማብዛት፣ የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ (e-Visa) አሰጣጥ መዘመኑ እና ወደ ተለያዩ የመዳረሻ አካባቢዎች የሚደረጉ የትራንስፖርት አማራጮች መቃናታቸው ጎብኚዎች ያለ ምንም እንግልት ሀገሪቱን እንዲጎበኙ መንገድ ከፍቷል። ይህም ሀገሪቱ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ለአፍሪካ እና ለዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ተፈላጊ ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል።

በተጨማሪም የዲጂታል ቱሪዝም ፕሮሞሽን እና የቅርሶች ጥበቃ ስራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፋቸው ለዘርፉ አዲስ ምዕራፍ አጎናጽፎታል።

በማህበራዊ ሚዲያ እና በዲጂታል አማራጮች የሚሰሩ ማስተዋወቂያዎች የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በአዲስ መልክ አስተዋውቀዋል።

እነዚህ የተቀናጁ የልማት፣ የጥበቃ እና የማስተዋወቅ ስራዎች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው አህጉር ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ራዕይዋን በተግባር እያረጋገጡት ይገኛሉ።

ይህንን የመንግስት ጥረት ተከትሎም ከባለሀብቶች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የዘርፉ ተዋንያን የሚመጣው ተሳትፎና የኢንቨስትመንት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል።

በአጠቃላይ እነዚህ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች፣ የታሪካዊ ቅርሶች ጥገና እና የተፈጥሮ መስህቦች ጥምረት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገት እና ለዘላቂ ልማት ያለውን ድርሻ ወደ ላቀ ደረጃ እያሳደጉት ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም