ቀጥታ፡

ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባትና ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባትና ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወጣት ፉአድ መሀመድ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ዜጎች እርስ በእርስ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት የሚፈጥሩበት አውድ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

ይህንንም ኢትዮጵያ ባካሄደችው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማሳካት መቻሏን ተናግሯል።

የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን በፖለቲካው ዘርፍ ከሚሰሩ ተግባራት ባለፈ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው በፍጥነት ተጠናቆ የተመረቁበት እና አዳዲስ ደግሞ የተጀመሩበት ሁኔታ መኖራቸው ለሀገር እድገት ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስቷል።

ለአብነት በሀገር እና በህዝብ ጥረት ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የሕዳሴ ግድብ በማንሳት ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲሻሻል እና ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ያደረገ መሆኑን የሚያኮራ ተግባር ነው ሲል ገልጿል።

ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንደሆነም ተናግሯል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ራህመት ዲኖ በበኩሏ፤ ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ በማካሄድ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ማረጋገጧን ገልጻለች።

እኛ ዜጎችም ከመንግሥት ጋር በጋራ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በላቀ ደረጃ እንዲቀጥሉ ተሳትፏችንን ልናጠናክር ይገባል ብላለች።

የሀገርን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ ልማትን ለማፋጠን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ዘሪሁን ፍቃዱ ነው።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ በሆነና ህዝቦችን በነቂስ ባሳተፈ መንገድ መከናወኑ የዴሞክራሲ አካሄዳችን እየዳበረ መሆኑን ማሳያ ነው ብሏል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ዮናስ ደስታ በበኩሉ፤ መንግሥት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በማጠናቀቅ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየወሰደ ያለው ቁርጠኛ እርምጃ የሚደነቅ ነው ብሏል።

ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት እየተጣለ መሆኑ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ብርሀኑ የሚያደርግ ተጠቃሽ እርምጃ መሆኑንም ተናግሯል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ ሕዝቡ በልማቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን በመንግሥት የሚደረጉ ጥረቶች ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም