ቀጥታ፡

ሊቨርፑል ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ፡- የዕለቱ ተጠባቂ ግጥሚያዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 8 : 30 ላይ ሊቨርፑል ከኖቲንግሃም ፎረስት በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሊቨርፑል በመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል።

በአንጻሩ ኖቲንግሃም ፎረስት በሜዳው በሊድስ ዩናይትድ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።

ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ከዚህ ቀደም 15 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሊቨርፑል በስምንቱ ሲያሸንፍ ፎረስት አራት ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ሊቨርፑል በ15ቱ ጨዋታዎች ላይ 20 ጎሎችን ሲያስቆጥር ኖቲንግሃም ፎረስት 13 ግቦችን አስቆጥሯል።

ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው ሊቨርፑል ሶስት ጊዜ ድል ሲቀናው ፎረስት አንድ ጨዋታ አሸንፏል። በቀሪው መርሐ ግብር ነጥብ ተጋርተዋል።

ሁለቱም ክለቦች ዛሬ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ።

በሌሎች መርሐ ግብሮች አዲስ አዳጊዎቹ ኮቨንተሪ ሲቲ ከሁል ሲቲ እና ቦርንማውዝ ከኤቨርተን በተመሳሳይ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከኒውካስትል ዩናይትድ  ጋር በቶተንሃም ሆትስፐርስ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ባለሜዳው ቶተንሃም በመጀመሪያው ጨዋታ በብሬንትፎርድ የ3 ለ 0 ሽንፈት ሲያስተናግድ ኒውካስትል ከሊቨርፑል ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል።

ቡድኖቹ የአዲሱን የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም