ኢትዮጵያ እንደ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ የባሕር በር ጥያቄዋንም ማሳካት የምትችል ታላቅ ሀገር ናት - ኡስታዝ ጀማል በሽር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እንደ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ የባሕር በር ጥያቄዋንም ማሳካት የምትችል ታላቅ ሀገር ናት - ኡስታዝ ጀማል በሽር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁሉ የባሕር በር ጥያቄዋን ማሳካት የምትችል ታላቅ ሀገር መሆኗን የዓባይ ንጉሶች ሚዲያ ባለቤት ኡስታዝ ጀማል በሽር ተናገሩ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶቿን በራሷ አቅም አልምታ መጠቀም እንደምትችል ያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኡስታዝ ጀማል በሽር፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተሳሰር ትብብርን ከማጠናከር አኳያ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያላት ትብብር በጋራ ተጠቃሚነትና ልማት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተግባር ማሳየቱንም ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም የሚከለክላት ማንም አካል እንደሌለ ጠቅሰው የሀገሪቷ የመልማት መብት ዓለም አቀፍ ህጎችና መርሆዎችን ያከበረ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ተጠቅማ በቀጣይ ለማከናወን ያሰበቻቸው ስራዎች ሀገሪቷን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
እየተጠናቀቁ ያሉ የመስኖ ግድቦች፣ አብዛኛው ስራ የተጠናቀቀው የኮይሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክትና ሌሎች ስራዎች የኢትዮጵያን የልማት ውጥን እውን የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ያሰበቻቸውን እያሳካች መሆኑን ጠቅሰው፤ በከተማ ልማት፤ ቱሪዝም እንዲሁም በምክክር የመግባባት ዴሞክራሲን በመገንባት ረገድ ውጤታማ ስራ እያከናወነች ስለመሆኑ አብራርተዋል።
አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ የሆነውን የባሕር በር ጥያቄ በይፋ አንስታለች ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ እና በፍትሃዊነት የመልማት ጥያቄ መሆኑን በማንሳት፤ ይህንን ማሳካት ደግሞ የትውልዱ የማይቀር እውነት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ አይቀሬ መሆኑን ጠላት ሳይቀር እየመሰከረው ያለው ሃቅ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሕዳሴ ግድብ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች ሁሉ የባሕር በር ጥያቄዋንም ማሳካት የምትችል ታላቅ ሀገር ስለመሆኑም ኡስታዝ ጀማል ተናግረዋል።