የምክክር መድረኩ የቆዩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሀገርን የማሻገር ፅኑ ፍላጎት የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር መድረኩ የቆዩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሀገርን የማሻገር ፅኑ ፍላጎት የታየበት ነው
ጂንካ፤ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ) ፡-ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የቆዩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሀገርን የማሻገር ፅኑ ፍላጎት የታየበት መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የተሻለች ሀገርን የመገንባት አዲስ ተስፋን የፈነጠቀና ለችግሮች በውይይት መፍትሔን በመሻት ሀገርን የማሻገር አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የተከፈተበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
በመድረኩ ላይ የተደመጡት የጋራ እይታዎች፣ የሰጡት ገንቢ አስተያየቶችና የታየው የነቃ ተሳትፎ ህዝቡ ያለፉ አለመግባባቶችን በመሻገር ወደ ተሻለ የታሪክ ምዕራፍ ለመሸጋገር ያለውን ፅኑ ፍላጎትና የጋራ ቁርጠኝነት ግልጽ አድርጎ ያሳየ ነበር።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የጂንካ ከተማ ነዋሪዎችም፤ የምክክር መድረኩ የቆዩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሀገርን የማሻገር ፅኑ ፍላጎት የታየበት ነው ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጋሻው ገላው፤ ምክክር ለሀገር ብቻ ሳይሆን በግል ህይወትም ችግሮችን ቀርፎ የተሻለ ህይወት ለመምራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር መድረኩ አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር የመፍታት መሠረት መጣሉን የጠቆሙት አቶ ጋሻው፤ ተነጋግሮ የመግባባት ባህል እንዲጎለብት ማስቻሉንም ገልጸዋል።
መሰረቷ የፀናች ህብረ-ብሔራዊት ሀገርን ለመገንባት የእያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ያነሱት ደግሞ አቶ ቅዱስ መንገሻ ናቸው።
በሀገራዊ የምክክር መድረኩ የተነሱ ሀሳቦች ብዙሃኑን ያማከሉ፣ አካታችና ሀገር የሚያሻግሩ በመሆናቸው፤ ለተፈጻሚነታቸው ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሀገርን ማሻገር ከተፈለገ ከግል ፍላጎት ይልቅ የሀገርን ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም እንደሚገባም አብራርተዋል።
"ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት ዕድል በማጣታችን በጥቃቅን ጉዳዮች አለመግባባት ውስጥ የምንገባበት ጊዜ አብቅቶ አዲስ የዲሞክራሲ ምህዳር ተፈጥሯል" ያሉት ደግሞ ሌላው የጂንካ ከተማ ነዋሪ አቶ እሸቱ ፈይሳ ናቸው።
የምክክር መድረኩ የሀሳብ የበላይነት የታየበትና ሀገርን ወደ ለውጥ ምዕራፍ ለማሻገር በህዝቡ ውስጥ ያለውን ጉጉትና ፅኑ ፍላጎት ያየንበት ነው ብለዋል።
በምክክር መድረኩ የተነሱ ሀሳቦች ተፈጻሚ ሆነው የታለመው ሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።