ቀጥታ፡

በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ያመጣነው ውጤት በቀጣይ ለተሻለ ስኬት እንድንሰራ የሚያነሳሳ ነው- ተማሪዎች

ጎንደር ፤ነሐሴ 22 /2018 (ኢዜአ)፡- በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ያመጣነው ውጤት በቀጣይ ለተሻለ ስኬት እንድንሰራ የሚያነሳሳ ነው ሲሉ በጎንደር ከተማ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ተናገሩ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ በበኩሉ  የዘንድሮው ዓመት በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በከተማዋ የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጿል።

በከተማዋ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት መካከል 63 ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸው ተገልጿል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ተማሪዎች እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት  ያገኝነውን ጥሩ ውጤት እንደመነሻ በመጠቀም  የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን በተሻለና ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በአገር አቀፍ  ደረጃ በተሰጠው የ12ኛው ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንካራ ዝግጅት አድርጎ 576 ነጥብ 4 ውጤት  ማምጡትን የተናገረው ደግሞ የአዘዞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ዳግም በሪሁን ነው።

የአዳር የጥናት ፕሮግራም ፣ የመምህራን ድጋፍ እና የቤተሰብ እገዛ ለውጤቱ መመዝገብ ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉለት መሆኑን ነው የገለፀው። 

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ትምህርት ቤት ተማሪ ናትናኤል ሙላት በበኩሉ፤ በሀገር አቀፍ ፈተናው 570 ነጥብ 1 ውጤት ማምጣቱን ተናግሯል።

ውጤቱን ለማስመዝገብ ሙሉ ጊዜውን ለትምህርት እና ለጥናት  ከመስጠቱ በተጨማሪ  የቤተሰብ ድጋፍ  መኖሩ ስኬታማ እንዳደረገው ነው የሚናገረው።


 

የጎንደር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ነጋሽ በበኩላቸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው የ12 ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ነው ያሉት ።

ባለፈው ዓመት በተሰጠው አገር አቀፍ 12ኛ ክፍል ፈተናም ከ500 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር 30 እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ከእጥፍ በላይ በመጨምሮ ቁጥራቸው 63 መድረሱን ነው የገለጹት።

ለውጤቱ መመዝገብም  የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱ ፣የቤተ መፅሐፍ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ መቅረቡ፣ የጥያቄና መልስ ውድድሮች መዘጋጀታቸው ፣ የአዳር ጥናት መኖሩና ከወላጆቻቸው ጋር በቅንጅት መሰራቱ  የራሱ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

በክልሉ ሁሉንም  ተፈተኝ ተማሪዎቻቸውን ካሳለፉ 8 ትምህርት ቤቶች መካከል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል። 

በቀጣይነትም በሁሉም የትምህርት እርከኖች  የሚገኙ የተማሪዎችን ውጤትና የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ግብዓትን የማሟላት፣ የመማር ማስተማር ስራውን ምቹ የማድረግ እና የትምህርት መሰረተ ልማቶችን የመገንባት ትኩረት የሚሰጣቸው እንደሆኑም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም