ቀጥታ፡

የኢትዮጵያውያን የወል እውነት- ሀገራዊ ምክክር

በሙሴ መለስ

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የጋራ መኖሪያ እና የብዝሃነት ውበት ደምቆ የሚታይባት ሀገር ናት ።

ዛሬ ላይ ለመድረስም በርካታ ውጣ ውረዶችን፣ እና የታሪክ ምዕራፎችን ተሻግራለች። በነዚህ ምዕራፎች ውስጥም በአብሮነትና በጋራ ሃገራዊ እሳቤ ከተገነቡት የጋራ ማንነቶች ባልተናነሰ መልኩ ያጋጠሙ የታሪክ ስብራቶች የልዩነት እና ያለመግባባት መንስኤ የሚሆኑበትን አጋጣሚም አስተናግዳለች።

ልዩነቶችን በጉልበት ወይም በኃይል ሳይሆን፣ በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር እና ከነጣይ ትርክት ይልቅ ወደ ሃገራዊ መግባባትና የጋራ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣትም ሃገራዊ ምክክሩ የራሱን ቁልፍ ሚና በመወጣት በሃገራችን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ይታወቃል።

ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ህዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ የህብረተሰቡን አጀንዳዎች በባለቤትነት የማሰባሰብ ሂደቱን በስኬት አከናውኗል።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራን፣ ዳያስፖራዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በአንድ መድረክ የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለ46 ቀናት ተካሄዶ በስኬት መጠናቀቁ ተበስሯል።

ይህ ጉባኤ ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የገለጹበት፣ የጋራ መግባባት ላይ የደረሱበት በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥም የጠመንጃ የበላይነትን በማስቀረት፣ የሀሳብ የበላይነትና የሰላማዊ የውይይት ባህልን ለማስፈን ምቹ ምህዳር የፈጠረ አካታች አካሄድ ነው።

ከጉባኤው የተገኙ ምክረ-ሐሳቦችና የተገኙት ልምዶች ወደ ተግባር እየተሸጋገሩ፣ በየደረጃው በሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ውይይቱ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትም ነው።

የጋራ ትርክት ህዝቦች በታሪካቸው፣ በአሁኑ ሁኔታቸው እና በወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ላይ ያላቸው የጋራ መረዳትና ስምምነት ሲሆን ይህም አብሮነትን ለማጎልበት ጠንካራ መሰረት ይጥላል።

ለዘመናት በጦርነት፣ በኃይልና በፖለቲካ ሽኩቻ ሲንከባለሉ የቆዩ የትርክት ስብራቶችም ከጠመንጃ ይልቅ በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ክርክር ለመፍታት ስለመቻሉም ትልቅ ማሳያ ነው።

በምክክሩ ላይ በመላው ሃገሪቱ አሉን የሚሏቸውን ጥያቄዎችና ቅሬታዎች በኃይል በጦር መሳሪያ ለመፍታት ነፍጥ አንግበው ሲታገሉ የነበሩ አካላት ሁሉ እንዲሳተፉ መደረጉም የሒደቱን ስኬታማነት ለዓለም ማህበረሰብ ያሳየ ነው።

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፣የፖለቲካ አመለካከቶችና የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አራት ሺህ ተመካካሪዎች የየራሳቸውን የተናጠል ፍላጎት ብቻ ከማንጸባረቅ ተቆጥበው በተለዩ ስምንቱ አበይት አጀንዳዎች ላይ በጋራ መስማማታቸውም የወል ትርክት ግንባታን የውጤታማነት ጉዞ ስኬት በተግባር የገለጠ ነው።

ይህ ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሳይሆን ለሀገር ህልውና እና ለጋራ ዕድገት ቅድሚያ የመስጠት ትልቅ የፖለቲካ ብስለትም ነው።

ይህ ሂደት እያንዳንዱ ዜጋ በሀገሩ ላይ ሙሉ ባለቤትነትና ደህንነት እንዲሰማው የሚያደርግ ሲሆን የጋራ አገርና የጋራ ዕድል አለን የሚለውን እሳቤ በማጉላትም የወል ትርክትን በጽኑ መሠረት ላይ ይገነባል።

ምክክሩ በጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን (Elites) መካከል ብቻ የተደረገ ውይይት ሳይሆን እስከ ወረዳ ድረስ ያሉትን የታችኛውን የህብረተሰብ ክፍሎች፣ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ መሆኑም ትልቅ ትርጉም አለው።

ከሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ የፈለቁት ምክረ ሀሳቦች ለሀገራዊ ትርክት መጠንከር ወሳኝ ሚና ከመጫወት ባለፈ ሂደቱ በህዝቡ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ያደርገዋል።

ምክክሩ ያረጋገጠው ትልቁ እውነት የኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ የተሳሰረ መሆኑንና የወል ትርክት ግንባታ የሀገር ህልውና ዋስትናነቱን ነው።

ልዩነቶችን ውበት፣ ውይይትን ደግሞ መሳሪያ በማድረግ የተጀመረው ይህ ጉዞ ኢትዮጵያ በቀደመ ታሪኳ የገጠሟትን የታሪክ ስብራቶች በመጠገን ወደ ዘላቂ ብልጽግና፣ ዲሞክራሲና እውነተኛ አንድነት እንድትሸጋገር ያስችላታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም