ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመኖሪያ ቤት ችግራችንን ፈቷል -በካፋ ዞን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች

ቦንጋ ፤ነሃሴ 22/2018 (ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን እንደፈታላቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ የካፋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

"በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ የሚገኘው የ2018 ዓ.ም የክረምት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን የካፋ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰው ተኮር ከሆኑ የመንግሥት ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፣ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በማገዝ ዘርፈ-ብዙ ችግሮችን እያቃለለ ይገኛል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የካፋ ዞን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን እንደቀረፈላቸው ተናግረዋል።


 

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል የቦንጋ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ወይኒቱ ወጋየሁ፤ ይኖሩበት የነበረው ቤት ያረጀ በመሆኑ ለመኖር ምቹ እንዳልነበር ገልጸው፣ አሁን በበጎ ፈቃደኞች ቤታቸው በአዲስ መልክ በመገንባቱ ከችግር መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ቤት ገንብቶ ከመስጠት ባሻገር የቤት ዕቃ እና የአልባሳት ድጋፍ እንደተደረገላቸው የጠቀሱት ወይዘሮ ወይኒቱ፤ ደስተኛ ሕይወት እየኖሩ በመሆኑ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ሌላኛዋ ተጠቃሚ በገዋታ ወረዳ የቆንዳ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቄ አለሙ በበኩላቸው፤ መንግሥት ባመቻቸላቸው ቦታ ላይ በጎ ፈቃደኞች ቤት ገንብተው እንደሰጧቸው ተናግረዋል።


 

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት በጎ ፈቃደኛው አቶ ተማም ከበደ፤ የወይዘሮ ወርቄ አለሙን ቤት ያለምንም ክፍያ በራሳቸው ተነሳሽነት ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበር በሙያቸው መገንባታቸውን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ከይሩ መሐመድ ዘይን በበኩሉ፤ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጿል።


 

የካፋ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ መዓዛ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በቤት እድሳትና ጥገና፣ በአካባቢ ጽዳትና በአረንጓዴ አሻራ፣ በደም ልገሳ እና በሌሎች 14 መስኮች አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከ943 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ሥራ በተገባበት በዚህ ተግባር፣ እስካሁን ከ870 ሺህ 335 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኅብረተሰቡ ዘንድ ባህል እየሆነ መምጣቱን ያነሱት ኃላፊዋ፤ መጪዎቹን በዓላት ታሳቢ ያደረጉ ማዕድ የማጋራት ተግባራትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም