ቀጥታ፡

ዲላ ዩኒቨርሲቲ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

ዲላ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፡-ዲላ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ለችግሮች ተግባር ተኮር ምላሽ ከመስጠት ባለፈ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በዲላ ከተማ፣ በጌዴኦ ዞን እና በአጎራባች ወረዳዎች የሰባት አቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታ ሥራን ዛሬ አስጀምሯል።


 

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ቶሎሳ ዳዲ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰራ ነው።

በተለዩ የትኩረት ዘርፎች በሚያካሂደው ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ለችግሮች ተግባር ተኮር ምላሽ ከመስጠት ባለፈ በበጎ ፍቃድ ሥራዎች በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን አንስተዋል።

በዛሬው እለትም በዲላ ከተማ፣ በጌዴኦ ዞን እና አጎራባች ወረዳዎች ሰባት የአቅመ ደካማ ወገኖች መኖሪያ ቤት ግንባታ ሥራ ማስጀመሩን ተናግረዋል። 


 

ከዚህ በተጨማሪ በዲላ ከተማ ለሚገኙ 200 ታዳጊ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና የግል ንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶችን ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ትስስርን በማጎልበት እርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን እንደሚያጠናክር ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራቸውን ሥራዎች ያጠናክራል ብለዋል።

በከተማው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል እየሆነ መምጣቱ ለበርካታ አቅመ ደካማ ዜጎች ሕይወት መለወጥ መሰረት ሆኗል ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የዲላ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ የካቲት ጥላሁን ናቸው።


 

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በከተማው ህብረተሰቡን በማስተባበር ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ለማቅረብ እየተሰራ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የዛሬው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም ይህንኑ የሚያጠናከር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የ232 አቅመ ደካማ ወገኖች መኖሪያ ቤቶች ግንባታና ጥገና እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማው "ዳማ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት" የ5ኛ ክፍል ተማሪ ጽዮን ታደሰ ድጋፉ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርቷን በአግባቡ ለመከታተል የሚያስችላት በመሆኑ ምስጋናዋን አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም