ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ ትሰራለች- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከየታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሮቹ የሁለቱን ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት በኢትዮጵያና ታይላንድ መካከል ያለውን የዲፕሎማሲና ፖለቲካ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማሳደግ የሚያስችል ገንቢ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉዋንግኬትክየው በበኩላቸው፤ ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ትብብር ማጠናከር ትፈልጋለች ብለዋል።

የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን በማጠናከር ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላት እምቅ አቅም ላይ እሴት መጨመር የሚያስችል ልምዳችንን እናካፍላለን ብለዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ታይላንድ በቅርቡ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ በመክፈት ትብብሯን ወደ ላቀ ደረጃ ታሸጋግራለች ብለዋል።

የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉዋንግኬትክየው ለይፋዊ የስራ ጉብኝት እና ታሪካዊውን “የታይላንድ-አፍሪካ ኢኒሼቲቭ” በይፋ ለማስጀመር አዲስ አበባ የገቡት ዛሬ ማለዳ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም