የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ድርሻ አለው-ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ድርሻ አለው-ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ለክልሉ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለአምራቹ ተጠቃሚነት ወሳኝ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
በደቡብ ጎንደርና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት የዘር ብዜትና ግብይት ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዮኖችን የማዋሃድ ስራ ዛሬ ተካሂዷል።
የክላስተሩ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ዩኒዮኖቹን ወደ አንድ የማዋሀድ ስራ የተካሄደው በሁሉም መስክ አቅም ፈጥረው የተጣለባቸውን ተልእኮ በተሻለ መልኩ እንዲወጡ ለማድረግ ነው።
የጉና እና የዕድገት የዘር ብዜት የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች መዋሃዳቸው ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም በመፍጠር የአርሶ አደሩን የዘር አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የተዋሃዱት ዩኒየኖች ‘‘አንድነት የዘር ብዜትና ግብይት ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን'' ተብለው የተቋቋሙ ሲሆን የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የጎላ ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል።
በተለይ ከበቆሎ ምርጥ ዘር በተጨማሪ የተለያዩ የሰብል ዘሮችን በጥራት አባዝተው ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርቡ ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደ የሪፎርም ስራዎች 388 ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበራትን 141 ሆነው እንዲዋሃዱ በማድረግ ፋይናንሻል አቅማቸውና የአመራር ብቃታቸውን ጠንካራ እንዲሆን ተደርጓል ያሉት ደግሞ የክልሉ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት አማረ ናቸው።
እንዲሁም 19 የህብረት ስራ ማህበራት ዪኒየኖችን ወደ 9 ዩኔዮኖች እንዲዋሃዱ በማድረግ የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጠናከርና በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ መከናወኑን ኮምሽነሩ አመልክተዋል።
በዛሬው ዕለትም በዘር ብዜት ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩትን የ''ጉናና የዕድገት ዘር ብዜትና ግብይት ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች' ውህደት መፈፀማቸው ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል።
በቀጣይም ኮሚሽኑ ሌሎች ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዮኖችን በማሰባሰብ ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ የሪፎርም ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የአንድነት የዘር ብዜትና ግብይት ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዮን የቦርድ ሰብሳቢ አርሶ አደር ደሴ ተረፈ፤ ውህደቱ አሰራርን በማዘመንና ምርትና አገልግሎታቸውን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደርን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በክልሉ ከ32 ሺህ የሚበልጡ ህብረት ስራ ማህበራትንና 61 ዩኒዮኖችን ለማዋሃድ እንደሚሰራም ነው የጠቀሱት።