የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን የድንበር ላይ አሰራሮችን የሚያሳልጥ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል - የአፍሪካ ሕብረት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን የድንበር ላይ አሰራሮችን የሚያሳልጥ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል - የአፍሪካ ሕብረት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን የሀገራትን የድንበር ላይ አሰራሮችን የሚያሳልጥ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ ሕብረት ገለጸ።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንና የዓለም ባንክ ያተዘጋጁ''አፍሪካን ማቀናጀት፤ ከተበታተኑ ትስስሮች ወደ ኢኮኖሚያዊ ማዕከላት'' የተሰኘ አዲስ አህጉራዊ የጥናት ሪፖርት ይፋ ሆኗል።
የጥናት ሪፖርቱም የአፍሪካን ከቀረጥ ነፃ የንግድና የምርት ትስስር በማጠናከር የአህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን በዘመናዊ መሠረተ ልማት በማስደገፍ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ ውህደት ማጠናከር እንደሚገባ አመላክቷል።
በሕብረቱ ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር ፍራንሲስካ ታቾፕ ቤሎቤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ አፍሪካ በተሰናሰለ አሠራርና መሠረተ ልማት የሚመራ የኢኮኖሚ ውህደትን ማሳለጥ ያስፈልጋታል።
ይህም የአህጉሪቱን የተበታተነ የገበያና የግብይት ሥርዓት ውጤታማነት በማሻሻል አፍሪካን የጠንካራ ኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ውህደት በሚፈረሙ ስምምነቶች ብቻ አይሳካም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠንም የሀገራትን የድንበር አሠራሮችን የሚያሳልጥ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካን አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የትብብር ማዕቀፍ በውጤታማነት በመተግበር የአህጉሪቷን ዜጎች የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማፋጠን እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም የአህጉሪቷን አባል ሀገራት የድንበር ላይ መተላለፊያ፣ ጉምሩክ፣ ታሪፍና የዲጂታል ክፍያ እንቅፋቶችን ማስወገድ የሚያስችል ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአህጉሪቷን የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳለጥ የሚደረጉ ጥረቶችም ጥሬ ዕቃን ከመላክ የተላቀቀ የኢንዱስትሪ፣ የኃይልና የትራንስፖርት እሴት ሰንሰለት የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
ይህም የበለፀገችና የተሳሰረች አፍሪካን የመገንባት የአጀንዳ 2063 ራዕይን በማሳካት የአፍሪካዊያንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሻሽል የኢኮኖሚ ምኅዳር መፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ምክትል ፕሬዝዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአፍሪካ የተቀናጀ መሠረተ ልማትና የሎጂስቲክስ ሥርዓት ለኢኮኖሚ ውህደት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአህጉሪቷን የኢኮኖሚ ውህደት ለሚያሳልጥም የተቀናጀ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን በመገንባት የአርሶ አደሩን፣ የኢንዱስትሪና ገበያን በቀጥታ የሚያገናኝ ምኅዳር መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የመሠረተ ልማቶች ትስስር አህጉራዊ የግብርና ገበያዎችንና የፋብሪካ ምርቶችን በማጠናከር ለአፍሪካውያን ሰፊና ዘላቂ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቅሰዋል።
የዓለም ባንክ የንግድ እንቅፋቶችን በመቀነስ፣ የድንበር ተሻጋሪ አሠራሮችን በማቃለል የአፍሪካን እውነተኛ የኢኮኖሚ ውህደትና የሥራ ዕድል በሚፈጥሩ መሠረተ ልማቶች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።