አዲስ አበባን የባህልና የዕደ-ጥበብ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን የባህልና የዕደ-ጥበብ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ) ፦አዲስ አበባን የባህልና የዕደ-ጥበብ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት ዘርፉን የሚያነቃቁ ውጤቶች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በዕደ-ጥበብ ዘርፍ ባሉ ተግዳሮቶች፣ የመፍትሔ አቅጣጫዎችና መልካም አጋጣሚዎች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቢሮው ምክትል ሀላፊ አዲሱ ሻንቆ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የውይይቱ ዋና ዓላማ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች የሚያጋጥሟቸውን ማነቆዎች በመለየት ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴዎች አዲስ አበባን የባህልና የዕደ-ጥበብ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሆናት ጠቅሰዋል።
የተከናወኑ የልማት ስራዎች የዕደ-ጥበብ ውጤቶች ባህላዊና ታሪካዊ እሴታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል ብለዋል።
አምራቾች ምርቶቻቸውን በሰፊው እንዲያስተዋውቁ፣ የገበያ ዕድል እንዲያገኙና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ከማስቻሉም በላይ አዳዲስ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ማገዙን ተናግረዋል፡፡
ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጥብቅ በመቀናጀት አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀላሉ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች የሚያቀርቡበት የገበያ መሰረተ ልማት መመቻቸቱን አንስተዋል፡፡
የዕደ-ጥበብ ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ዘርፉ ለከተማዋ ኢኮኖሚ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተጀመሩት የተቀናጁ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ በዕደ-ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች መንግስት እያደረገላቸው ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍና ክትትል የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የመስሪያ ቦታ፣ የብድር አቅርቦትና የገበያ ትስስር በማመቻቸት በኩል የተደረጉት ድጋፎች ለስራቸው ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው አምራቾች መካከል የሰውልክ መንግስቱ፤ በመዲናዋ የተከናወኑት የልማት ስራዎች ምርቶቻቸውን ለህብረተሰቡና ለጎብኚዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግና የገበያ እድላቸውን ለማስፋት እንደረዳቸው ገልጻለች።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ብርሀኑ ገብረእግዚአብሄር በበኩሉ፤ ቢሮው ተከታታይ ስልጠናዎችን በማመቻቸት የሙያ አቅማቸውንና የምርት ጥራታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ እያገዛቸው መሆኑን ጠቁሟል።
በመንግስት በኩል የተመቻቹት የብድር አቅርቦቶችና የገበያ ማዕከላት፣ የተለያዩ የሸክላ ምርቶችን በጥራት አዘጋጅተው ለደንበኞቻቸው እንዲያቀርቡ ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸው የተናገረችው ደግሞ መአዛ አሰግድ ናት፡፡