ቀጥታ፡

የታይላንድ–አፍሪካ ኢኒሼቲቭ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብርን ለማጠናከር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፦ የታይላንድ–አፍሪካ ኢኒሼቲቭ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብርን ለማጠናከር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉአንግኬትኬኦ ገለጹ።

የታይላንድ-አፍሪካ የትብብር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉአንግኬትኬኦ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ታይላንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የስትራቴጂያዊ አጋርነት ለማሳደግ የሚያስችል አዲስ ማዕቀፍ ይፋ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ መድረክ ላይ የጉብኝታቸው ዋነኛ መነሻ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የተመሰረተው ይህ የትብብር ማዕቀፍ በተለይም ከአፍሪካ ኅብረት እና ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ECOWAS) ጋር ያለውን ተቋማዊ ትብብር በይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።

በተጨማሪም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር (ASEAN) መካከል ጠንካራ የኢኮኖሚ ድልድይ ለመፍጠር ታስቧል።

ዓላማውን ከዳር ለማድረስም የታይላንድ የንግድ ልዑክ በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ የመንግሥት እና የግል ዘርፍ ተወካዮች ጋር በመገናኘት የንግድ ማኅበረሰቡን የሚያስተሳስር ውይይት እንደሚያደርግ ተገልጿል።


 

በሌላ በኩል ታይላንድ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማጎልበት ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበር እና ሦስት ሚሊዮን ዶላር በጀት የተመደበለት አዲስ የድርጊት መርሐ ግብር ይፋ አድርጋለች።

መርሐ ግብሩ በዋናነት በግብርና፣ በምግብ ዋስትና እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን፣ በተለያዩ የአፍሪካ አካባቢዎች የግብርና ማሠልጠኛ ማዕከላትን ለማቋቋም ይውላል።

በፈረንጆቹ 2028 የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር ሊቀመንበርነትን የምትረከበው ታይላንድ፣ በማኅበሩ እና በአፍሪካ ኅብረት መካከል በምግብ እና ኃይል ዋስትና እንዲሁም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዙሪያ ያለውን ዘርፈ ብዙ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሠራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም