ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ትልቅ አቅምን የፈጠረ ነው- የጽህፈት ቤቱ አባላት

ደሴ፤ ነሐሴ 22/2018(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ትልቅ አቅምን የፈጠረ ነው ሲሉ  የደቡብ ወሎ ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ጽሕፈት ቤት አባላት ገለጹ።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር እና መሠረታዊ በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ሲካሄድ የቆየው ሀገራዊ የምክክር ሂደት በስኬት ተጠናቋል።

በሂደቱ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ አካላት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች እና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ረገድ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተ ሆኖ ተገኝቷል።

በዚህም የተገኙ ውጤቶችና የቀረቡ የፖሊሲ አስተያየቶች ወደፊት ለሚከናወኑ ሀገራዊ የሪፎርም ሥራዎች እና ለዘላቂ ውሳኔዎች መሠረት የሚሆኑ ናቸው።

የጽሕፈት ቤቱ ፀሐፊ ተተኪ አርበኛ አየለ ወልደ ጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የምክክር መድረኩ አሳታፊና አካታች መሆኑ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ክስተት ነው ።

ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን በንግግርና በውይይት  መፍታት እንድንችል በታሪክ የተገኘ መልካም አጋጣሚ ነው ሲሉም አመላክተዋል።

ችግሮችን በምክክር፣ በውይይትና በእርቅ መፍታት የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ውጤታማ ባህል መሆኑን አሁናዊው ሂደት ዳግም አስመስክሯል ነው ያሉት። 

ይህም በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ ዋልታ-ረገጥ ችግሮቻችንን በውይይት ፈትተን፣ለቀጣዩ ትውልድ  የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ትልቅ አቅም የሚፈጥር እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ከሕዝብ የተወከሉ ዜጎች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመካክረው ማጠናቀቃቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነትን የሚያጸና መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው የጽሕፈት ቤቱ አባል ሃምሳ አለቃ ባለሟል መለሰ በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ታሪካዊ ድል ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነም ገልጸዋል። 

ችግሮቻችንን በራሳችን ፍላጎትና አቅም መፍታት እንደምንችል ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተግባር ያረጋገጥንበት ነው ሲሉም አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ የተካሄደው ጉባኤ አካታችና አሳታፊ መሆኑ ለተመዘገበው ስኬት ዋና መሰረት እንደሆነም ነው የተናገሩት።

"ምክክሩ አንዱ የሌላውን ሀሳብና ችግር ተጋርቶ፣ ተሳስቦና ተጋግዞ በአንድነት መኖር የሚያስችለው ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው አባል ሃምሳ አለቃ አለማየሁ አበበ ናቸው። 

በቀጣይም የመመካከርና የመወያየት ባህላችንን በማስቀጠልና በማጎልበት ለዘላቂ ሰላማችንና አንድነታችን አስተማማኝ መሰረት መጣል አለብን ነው ያሉት።

አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም፤ በአዲስ አበባ በተካሄደው ጉባኤ ሁሉም ተመካካሪ የወከለውን ሕዝብና አካባቢ ይጠቅማል ያለውን ሀሳብ በነፃነት በማንሸራሸር መግባባት ላይ መድረሱ መልካም ጅምር መሆኑን ተናግረዋል።

በምክክር ጉባኤው ድምዳሜ ላይ የተደረሰባቸውን ውሳኔዎች መላው ሕብረተሰብ ተቀብሎ በመተግበር የሀገራችንን አንድነት ለማጽናት የድርሻችንን መወጣት አለብን ሲሉም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም