ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከልን ጨምሮ ከ35 በላይ የዲጂታል አሰራሮችን ለመዘርጋት ተችሏል- ቢሮው

ባህር ዳር፡ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከልን ጨምሮ ከ35 በላይ የዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት መስጠት መቻሉን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው ባለፉት ሦስት ዓመታት በዲጂታላይዜሽን ትግበራ በተመዘገቡ ውጤቶችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ዛሬመግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም  የመሶብ አንድ ማዕከላትን ጨምሮ የተለያዩ ዘመናዊ መተግበሪያዎችን በማልማት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።

የክልሉ መንግሥት በ25 ዓመት የስትራቴጂክና አሻጋሪ ዕቅዱ ለቴክኖሎጂው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት መሠረት፣ አገልግሎት በሚበዛባቸው ተቋማት ላይ በማተኮር ከ35 በላይ የዲጂታል አሰራሮች መዘርጋቱን ነው የገለጹት።

ቴክኖሎጂዎቹ  በፍትሕ ሥርዓት፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ ኢንቨስትመንት በመሳብና በግብርናው ዘርፍ ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻላቸውንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ቴክኖሎጂዎቹ የመንግሥት አካላት በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጡ ከማድረጋቸው ባሻገር፣ ይስተዋሉ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል።

በተለይም "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በክልል ደረጃ  በባህር ዳር፣ ደሴና ወልዲያ ከተሞች ተግባራዊ በማድረግ የህዝቡን እርካታ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

በተካሄደው የዳሰሳ ጥናትም እስካሁን ከ103 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በኩል ፈጣን ፣ ፍትሐዊና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት ማግኘታቸው መረጋገጡን አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅትም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋት የግንባታና የቴክኖሎጂ ዝርጋታ ሥራው እየተፋጠነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በቀጣይ ዓመትም የዲጂታል 2030ን ግብ ለማሳካት ተጨማሪ ከ13 በላይ አዳዲስ መተግበሪያዎችን የማልማት ስራ እንደሚከናወን አብራርተዋል።

በክልሉ በዲጂታል ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን ለህዝብ ለማስተዋወቅ ያለመ የፓናል ውይይትና የኤግዚቢሽን መርሃ-ግብር ከነሐሴ 28 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም