ቀጥታ፡

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባዔ ኢትዮጵያ በክትባትና በጤና ምርምር ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፦ 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባዔ ኢትዮጵያ በክትባትና በጤና ምርምር ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን ውጤታማ ተግባራት ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባዔ በትናንትናው ዕለት በስኬት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡

የጉባዔው ተሳታፊዎች በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የሚገኘውን የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትን በመጎብኘት በሥራ ላይ ያሉ አቅሞችንና የምርምር ሥራዎችን ተመልክተዋል፡፡


 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በጉባዔው በጤና ምርምር ዘርፎች ያስመዘገበቻቸውን ውጤታማ ተግባራት ለአህጉሩ ተወካዮች ማጋራት ችላለች፡፡

በመድረኩ በጤና መረጃ ሥርዓት ትንተና፣ በአቅም ግንባታ እና በክትባት ዙሪያ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች አጋርታለች ብለዋል፡፡

ተጨባጭ ስኬቶቿን እንድታሳይ ከማስቻሉም በላይ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የጠበቀ የላቦራቶሪና የምርምር ትስስር እንድትፈጥር ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የጋራ ልምድ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም እንዲሁ፡፡

በጉባዔው ወቅት የቀረቡት የምርምርና የአቅም ግንባታ ሥርዓቶች በቀጣይ ለሚከናወኑ ሀገራዊና አህጉራዊ የጤና ሥራዎች በበጎ መነሻነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ጉባዔው ለኢትዮጵያም ሆነ ለተሳታፊ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መልካም አጋጣሚ እንደነበር አብራርተዋል፡፡


 

በጋምቢያ የጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት ዳይሬክተር (ዶ/ር) ሞሞዶ ንያሲ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ሂደቱ እጅግ ፈጣንና በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለይ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ለአጠቃላይ የአፍሪካ አህጉር የሚመጥን ትልቅ የልህቀት ማዕከል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የህክምና ባለሙያዎቻቸውንና ተመራማሪዎቻቸውን ለልምድ ልውውጥ፣ ለምርምር፣ ለፈጠራ ሥራዎችና ለትምህርት ሊልኩበት የሚችሉበት ተስፋ ሰጪ ኢንስቲትዩት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካን የጤና አጀንዳ በተሻለ ደረጃ ለማሳካትና አህጉራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ከኢንስቲትዩቱ ጋር የጠበቀና የተቀናጀ የትብብር ግንኙነት ለመሥራት በጉጉት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም