በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናን በማዘመን የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናን በማዘመን የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ዱራሜ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናን በማዘመን የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ ።
"የተቀናጀ የግብርና ትጋት ለተመጣጠነ ምርታማነት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልላዊ የግብርና ሴክተር የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በዱራሜ ከተማ ተካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች ስኬት ተመዝግቧል።
የዘርፉን ስኬታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ለቴክኖሎጂና ለሰው ሀይል ልማት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
ይህም የአርሶ አደሩን የምግብ ሉአላዊነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋት እያገዘ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው በዞኑ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት አስገኝቷል።
አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም የማልማት ልምዱን ከማስፋፋት ባለፈ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ማደጉ በበቆሎ ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል።
በዘርፉ እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የአመራሩ፣ የግብርና ባለሙያውን እና የአርሶ አደሩ ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ አበራ ገልጸዋል።
የከምባታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ተሾመ ሄራሞ በበኩላቸው በዞኑ ከሰብል ልማት በተጨማሪ የቡና እና የቅመማ ቅመም ልማት እየተስፋፋ ነው።
ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ12ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ዝንጅብል መልማቱንና ለአርሶ አደሩም የገበያ ትስስር መፈጠሩን አንስተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።