ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት በማምረት ሚናቸው እያደገ መጥቷል

አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት በማምረት  ያላቸው ሚና እያደገ መምጣቱ ተገለጸ።

"የኢትዮጵያን ይግዙ" በሚል መሪ ሃሳብ ክልል አቀፍ የንግድ ባዛር እና ኤግዚቢሽን ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተከፍቷል።



በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በማምረት በኩል ያላቸው ሚና እያደገ መጥቷል።

በክልሉ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና በገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር  የኤክስፖርት ምርት አቅርቦትን በጥራትና በብዛት ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ እመርታ ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ህጋዊ የንግድ ስርአትና ተወዳዳሪነትን በማስፈን የክልሉን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት በተደረጉ ጥረቶች ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑንም አቶ ተፈሪ አስረድተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ገበያ ድርሻን ከማላቅ ባለፈ ህገ-ወጥነትን በመከላከል ጤናማ የገበያ ሰንሰለት ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን አቶ ተፈሪ አስታውቀዋል።


 

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ሰናይት ሰለሞን በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዋና ዋና ሀገራዊ ተልዕኮዎች የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በተለይ 22 መካከለኛ እና 134 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅም ማምረት እንዲችሉ መደረጉ ክልላዊ የማምረት አቅምን 63 በመቶ አድርሷል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ምርቶች ጥገኝነት የሚያላቅቁ ተኪ ምርቶችን በስፋት ማምረት እንደቻሉም ገልጸዋል።

በክልሉ በሚገኙ 105 የቅዳሜ እና እሁድ  ገበያዎች የግብርና፣ የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦትን በማሻሻል የገበያ ማረጋጋት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።


 

የአርባ ምንጭ "ኤሊያና ጋርሜንት" ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኤርሚያስ ደማ እና በወላይታ ሶዶ "ሰላሙ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ማህበር" ሰብሳቢ ዮናስ ቶማስ በንግድ ባዛርና ኤግዚቪሽኑ መሳተፋቸው ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ሰንሰለት ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ምርቶች በጥራትም ሆነ በንድፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እየሆኑ በመምጣታቸው ማህበረሰቡ የሀገሩን ምርት የመጠቀም ልምዱን ማሳደግ እንዳለበት አመልክቷል።

ክልል አቀፍ የንግድ ባዛርና ኤግዚቢሽኑ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የተለያዩ አምራቾች፣ አስመጪዎች፣ ላኪዎች እና ኢንዱስትሪያሊስቶች ምርቶቻቸውን በማቅረብ እየተሳተፉ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም