የስኬት መገለጫና የውጤት ማሳያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የስኬት መገለጫና የውጤት ማሳያዎች
አዲስ አበባ ነሀሴ 22/2018 (ኢዜአ) የስኬት መገለጫና የውጤት ማሳያዎች
በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብና የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (Homegrown Economic Reform) እቅዶችን በመተግበር በበርካታ ዘርፎች መሠረታዊ ለውጦችን እና ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል (አይሲቲ)፣ በማዕድን እና በቱሪዝም ዘርፎች የተመዘገቡት ስኬቶች የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ አቅም ከማሳደግ ባሻገር የወደፊት ዘላቂ እድገት መሠረት ያኖሩ መሆኑን መናገር ይቻላል። በመሆኑም በአምስቱ ዋና ዋና ሴክተሮች የመጡ ውጤቶችና የተመዘገቡ ስኬቶችን በወፍ በረር እንቃኛለን።
1. በግብርና ዘርፍ
የስንዴ ምርትና የውጭ ኤክስፖርት: የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መስፋፋት ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት አስቀምጧል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ሀገር መላክ የቻለችበትን እመርታዊ ስኬትም አሳይቶናል።
የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭን በመተግበር በወተት፣ በእንቁላል፣ በዶሮና የማር ምርት እንዲሁም በአትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ሩዝና ሻይ ልማትም ባለፉት አምስት አመታት እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል። አርሶ አደሩ የመሬትና የውሃ ሀብቶችን አቃፊ በሆነ መንገድ በመጠቀም በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ማምረት የሚችልበት አሰራር ተዘርግቷል። በዚህም የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ሁነኛ የገቢ ምንጭ የሆነበትን እድል ፈጥሯል። ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን የመቻል አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ የቡና ምርታማነትና ጥራት በማደጉ ምክንያት በኤክስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማገኘት ተችሏል።
በዘርፉ በቀጣይም የግብርናውን ዘርፍ ይበልጥ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሜካናይዜሽን በማስደገፍ ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። የመስኖ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የዝናብ ጥገኝነትን ለመቀነስ መጣር እንዲሁም የግብርና ምርቶችን ጥራት በማሻሻልና በማቀነባበር ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ዋጋ ማሳደግ ተገቢ ይሆናል።
2. የኢንዱስትሪ ዘርፍ
ሀገራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ንቅናቄ በመፍጠር ቀደም ሲል ተቆልፈው የነበሩና በዝቅተኛ አቅምያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ወደ ሙሉ የማምረት አቅማቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
የሀገር ውስጥ የምርት ፍላጎትን በመሸፈን ለውጭ ሀገር ምርቶች ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪም መቀነስ አስችሏል።
ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የህግና የአሰራር ሁኔታዎችን በመፍጠር በርካታ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ተችሏል። ከተገነቡት የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች (IAIPs) ጋር አርሶ አደሩን በማስሳሰር የግብአትና የምርት ትስስር እንዲጠናከር ተደርጓል። የአምራች ዘርፉ መስፋፋት ለብዙ ሺህ ዜጎች፣ በተለይም ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የታቸለበት ሆኗል።
በቀጣይም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በኃይል፣ በሎጂስቲክስና በግብአት አቅርቦት ሙሉ በሙሉ በመደገፍ ኤክስፖርትን ማሳደግ። የአምራች ኢንዱስትሪዎች 80% እና ከዚያ በላይ የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን እንዲጠቀሙ ማበረታታት፣ በህዝብና በግል አጋርነት (PPP) አማካኝነት በትልልቅ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ላይ የግሉን ዘርፍ አሳትፎ ማስፋፋት ትኩረት የሚደረግበት ይሆናል።
3. የዲጂታል (አይሲቲ) ዘርፍ
የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስልት ስኬቶችን በማስቀጠል ወደ "ዲጂታል 2030" እቅድ መሸጋገር ተችሏል። በ"መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና በሌሎች ፖርታሎች አማካኝነት ህዝባዊ አገልግሎቶችን በበይነ-መረብ (Online) የመስጠት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የዜጎችን መረጃ ማዕከላዊ የሚያደርግና ለፋይናንስ እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎቶች መሠረት የሆነውን የፋይዳ መታወቂያ ፕሮጀክት በላቀ መልኩ ማሳካት ተችሏል። የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የኮደር ስልጠናም የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ለማሳደግ ታላቅ ሀገራዊ የስልጠና መርሃ ግብር ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።የዲጂታል አገልግሎቶች መዘርጋታቸው የፊት ለፊት ግንኙነትን በመቀነስ ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን በመከላከል የኢንቨስትመንት ምህዳሩን አሳልጧል።
የቴሌኮም ዘርፍ ውድድር: የቴሌኮም ዘርፉን ክፍት ማድረግን ተከትሎ የኢንተርኔትና የኔትወርክ ተዳራሽነትንና ጥራትን በየገጠሩ የማስፋት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን እና የባንክ አገልግሎቶችን ይበልጥ ዘመናዊና የተቀናጁ ማድረግም አስፈላጊ ይሆናል። የሀገሪቱን የዲጂታል መሠረተ ልማት ከሳይበር ጥቃቶች የመጠበቅ አቅምን ማጠናከር።
4. የማዕድን ዘርፍ
በዘርፉ ይስተዋል የነበረውን ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ በመግታት ህጋዊ አሰራርና ቁጥጥር እንዲሰፍን ተደርጓል። የህግና መመሪያዎች ማሻሻያ በማድረግ የማዕድን ዘርፉን ለውጭና ሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ማራኪ የሚያደርጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። የወርቅ፣ የከሰል ድንጋይ፣ የሲሚንቶ ግብአቶችና የከበሩ ድንጋዮች ምርትን በማሳደግ ዘርፉ የሀገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ እንዲሆን ተሰርቷል። በተለይም የከሰል ድንጋይ ምርትን በሀገር ውስጥ አምርቶ በመተካት ለፋብሪካዎች ግብአት ማቅረብ ተችሏል።
5. የቱሪዝም ዘርፍ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር)አነሳሽነት የተጀመሩት "ገበታ ለሸገር"፣ "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክቶች በመላ ሀገሪቱ በርካታ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መገንባት ተችሏል።
በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የተከናወኑ የኮሪደር ልማቶች የከተሞችን ውበትና ለኑሮ ምቹነት ከመጨመራቸው ባሻገር ለከተማ ቱሪዝም ትልቅ እድል ፈጥረዋል። አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችንና ኮንፈረንሶችን ባካሄደችበት የዲፕሎማሲና የኮንፈረንስ ማዕከልነቷን አጠናክራለች።
የሀገሪቱን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የመጠበቅ፣ የማደስና ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል።
በድምሩ ባለፉት አምስት ዓመታት በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል፣ በማዕድን እና በቱሪዝም ዘርፎች የተመዘገቡት ስኬቶች ሀገሪቷን ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ማሸጋገር አስችለዋል። በመሆኑም እነዚህን ስኬቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል የታቀዱትን የወደፊት ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች በተቀናጀ መልኩ መተግበር፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና የግሉን ዘርፍ አሳታፊነት ማሳደግ በቀጣይ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ዋነኛ የቤት ስራ ይሆናል።