ቀጥታ፡

በዲላ ከተማ 551 የመንግሥት ቤቶች ተገንብተው ለቤት ፈላጊዎች ተሰጥተዋል

ዲላ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፡-በዲላ ከተማ ህብረተሰቡን በማስተባበር 551 የመንግሥት ቤቶች ተገንብተው ለቤት ፈላጊዎች መሰጠቱን የከተማው ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ።

በአስተዳደሩ ተገንብተው የተጠናቀቁ 50 መኖሪያ ቤቶች በዛሬው እለት ታዛቢዎች ባሉበት በእጣ ለተጠቃሚዎች ተሰጥተዋል።

የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ማዘንጊያ ኢያቶ በዚህ ወቅት እንዳሉት በከተማው የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማስፋት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው።


 

በ2018 ዓም ህብረተሰቡን በማስተባበር ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በተደረገ ጥረት  551 የመንግሥት ቤቶች ተገንብተው ለቤት ፈላጊዎች መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው እለትም ለባለዕድለኞች በእጣ የተሰጡት 50 መኖሪያ ቤቶችም የዚህ አካል መሆናቸውን ጠቅሰው ቤቶቹ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

በከተማው የቤት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ለግልና ለማህበር አልሚዎች በቂ መሬት መዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ በተለይ በቤት ልማት ለሚሰማሩ የግል ባለሃብቶች የተሟላ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር የነዋሪውን አንገብጋቢ ችግሮች በመለየት አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የዲላ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ የካቲት ጥላሁን ናቸው።


 

ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው በአሁን ወቅት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች የ157 አዲስ መኖሪያ ቤት ግንባታ እና የ75 ቤቶች እድሳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት ቤት ያገኙ ባለዕድለኞች የተረከቡትን ቤት በአግባቡ በመያዝና በማስተዳደር ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ዕጣው ከወጣላቸው ባለዕድለኞች መካከል የአካል ጉዳት ያለባቸው ወይዘሮ ጸሐይነሽ ዱኩሌ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ የኪራይ ቤት ማግኝት አዳጋች ሆኖባቸው መቆየቱን አንስተዋል።


 

በዚህም ለረጅም ዓመታት ለችግርና ለእንግለት ሲዳረጉ መቆየታቸውን አንስተው፣ ዛሬ በከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ ተሰጥቶ  የተሰጣቸው መኖሪያ ቤት ይህን ችግራቸውን እንደሚፈታ ተናግረዋል። 

መሰረተ ልማት የተሟላላት ባለሁለት መኝታ ቤት የመንግስት ቤት በማግኝታቸው መደሰታቸውንም ተናግረዋል።

በመንግስት ሥራ ከ32 ዓመታት በላይ ቆይተው በአሁኑ ወቅት በጡረታ መገለላቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ አቶ አየለ ዱቢሳ ናቸው።


 

የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ መሆናቸው የረጅም ጊዜ ችግራቸውን እንደቀረፈላቸው ተናግረው፤ ለከተማ አስተዳደሩ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም