በምስራቅ ወለጋ ዞን የክረምት እርሻ እና የልማት ኢንሼቲቮች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ወለጋ ዞን የክረምት እርሻ እና የልማት ኢንሼቲቮች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል
ነቀምቴ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ) :-በምስራቅ ወለጋ ዞን የ2018/2019 የምርት ዘመን የክረምት እርሻ እናየልማት ኢንሼቲቮች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ደረጄ ብርሃኑ(ዶ/ር) በምርት ዘመኑ የተሻለ ምርት ለማግኘት ከአቅርቦት ጀምሮ በተሰራ ስራ ከታቀደው በላይ ማሳ በዘር ተሸፍኖ የሰብል እንክብካቤ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም 801 ሺህ 185 ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ 831 ሺህ 816 ሄክታር በማረስ ከታቀደው በላይ 103.8 በመቶ ማሳካት መቻሉን ያሳያል።
አርሶ አደሩ የግብርና ፓኬጆችን በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ በተጀመረው የሙሉ ፓኬጅ ስራም፤ 210 ሺህ 635 ሄክታር በሙሉ ፓኬጁ ማረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
በልማት ኢኒሼቲቭ በተከናወኑ የክረምት ሰብሎች ስራም በቆሎ 134 በመቶ፣ ቦሎቄ 122 በመቶ፣ ኦቾሎኒ 106 በመቶ፣ እንዲሁም ማሽላና ስንዴ እያንዳንዳቸው 103 በመቶ በማረስ ከዕቅድ በላይ መፈጸም ተችሏል ብለዋል።
በሚገኘው የተሻለ ምርትም የራስ ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ ምርቱን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል።
በኩታገጠም እርሻም 642 ሺህ 62 ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን አስታውሰው፤ በዘርፉ በየጊዜው በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ እና በተደረገው የቅርብ ክትትል ለውጥ መመዝገቡንም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ከግብርና ግብዓቶች አቅርቦት ጋር ተያይዞ፣ ወቅቱን የጠበቀ የዘር እና የማዳበሪያ አቅርቦት ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ መሰራቱን ዶክተር ደረጄ ገልጸዋል።
የተዘራው ሰብል ለተፈለገው ምርታማነት እንዲበቃና ከአረም ጥቃት እንዲጠበቅ የአረም መድኃኒት አቅርቦት እና አጠቃቀም ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ዶክተር ደረጄ አክለው ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በሰብል ጥበቃ በተለይም ተባይ ቁጥጥርም 226 ሺህ 326 ሄክታር ተፈትሾ 42 ሺህ 823 ሄክታር ላይ የመቆጣጠር ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
በዞኑ የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች በበኩላቸው የግብርና እና ሌሎች የልማት ኢንሼቲቮችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተግተው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዞኑ የዲጋ ወረዳ አርሶ አደር አቶ ሰንበቶ ኢቲቻ በኩታገጠም እርሻ የተለያዩ ሰብሎችን እያለሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ባላቸው ከሁለት በላይ ሄክታር መሬትም የተሻለ ምርት ለማግኘት የግብርና ሜካናይዜሽኖችን እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር አዲሱ ግዛው በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉላቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከራሳቸው ጥረት ጋር በባለሙያዎቹ በመታገዝም የተሻለ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።