ተግባራዊ የተደረጉ የግብርና ቴክኖሎጂና የምርጥ ዘር አቅርቦቶች የአርሶ አደሩን ውጤታማነት እያሳደጉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ተግባራዊ የተደረጉ የግብርና ቴክኖሎጂና የምርጥ ዘር አቅርቦቶች የአርሶ አደሩን ውጤታማነት እያሳደጉ ናቸው
ሮቤ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፡- ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተግባራዊ የተደረጉ የግብርና ቴክኖሎጂና የምርጥ ዘር አቅርቦቶች የአርሶ አደሩን ውጤታማነት እያሳደጉ መምጣታቸውን ምሁራን ገለጹ።
መንግስት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ግብርናውን ከማዘመን ባለፈ ወቅትን ጠብቆ ብቻ ከማምረት ልምድ ለማውጣት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ተግባራዊ አድርጓል።
ይህም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ተረጂነትን ከማስቀረት ባለፈ የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ በኩል ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረገ ይገኛል።
ኢዜአ በመንግስት የግብርና ልማት እቅዶች ትግበራና ውጤታማነት ላይ ከዘርፉ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
ሞያዊ ማብራሪያ ከሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች መካከል የብሔራዊ የስንዴ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪና የቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ ነጋሽ ገለታ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የግብርና ልማት ትግበራ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀምና ወቅትን ጠብቆ ከማምረት ልምድ ለመውጣት የሚያስችል ነው።
የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውኃ አማራጮችን ጥቅም ላይ በማዋል አርሶ አደሩ ዝናብን ብቻ ከመጠበቅ ወጥቶ የመስኖ ልማትን በስፋት በመጠቀም ምርታማነትና ተጠቃሚነቱን እያሳደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የግብርና ልማቱን ውጤታማ እንዲሆን የአፈር ለምነትን ለማሳደግና እርጥበትን ተጠቅሞ ለማልማት የተደረጉ ጥረቶች ስኬት ማስገኘታቸውንም አንስተዋል።
በክልሉ ምርጥ ዘሮችን ከመጠቀም በተጨማሪ የኩታገጠም እርሻን ማስፋፋት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደጉን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ የአግሮኖሚ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደሳለኝ ደጀኔ ናቸው።
ለዚህም ኢንተርፕራይዙ የስንዴ፣ የገብስና የባቄላ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ ከማቅረብ ባለፈ በኩታገጠም አሰራር እና በሰብል እንክብካቤ ላይ ሙያዊ ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።
በምርጥ ዘር አቅርቦቱ በሽታንና ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተለይም ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምርጥ ዘር አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ተደራሽ በማድረግ ውጤታማነት ለማሳደግ መሰራቱን አመልክተዋል።
በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የስንዴ ምርምር ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጀማል አብዱልከሪም በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የመስኖ ስንዴን ልማትን ለማሳደግ አርሶ አደሮችን በሥልጠናና በግብዓት እያገዘ ነው።
በተለይም ለባሌ፣ ለምሥራቅ ባሌና ለምዕራብ አርሲ ዞን አርሶ አደሮች ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እውቀት እንዲያገኙ ስልጠና መሰጠቱን አስረድተዋል።
የግብርና ቴክኖሎጂና የምርጥ ዘር አቅርቦቶች ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን ውጤታማነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑንም አስታውቀዋል።