ግብፅ በዓባይ ወንዝ ምንም ዓይነት የውሃ ምንጭ አበርክቶ ሳይኖራት በኢትዮጵያ ላይ የምታቀርበው መሠረተ ቢስ ክስ ተቀባይነት የለውም - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ በዓባይ ወንዝ ምንም ዓይነት የውሃ ምንጭ አበርክቶ ሳይኖራት በኢትዮጵያ ላይ የምታቀርበው መሠረተ ቢስ ክስ ተቀባይነት የለውም
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፦ግብፅ በዓባይ ወንዝ ምንም ዓይነት የውሃ ምንጭ አበርክቶ ሳይኖራት በኢትዮጵያ ላይ የምታቀርበው መሠረተ ቢስ ክስ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው የውሃ ሀብት ተመራማሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ የተቸራትን የተፈጥሮ ጸጋዎች እንዳትጠቀም የዘመናት ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብፅ የውስጥ ባንዳዎችን በመቅጠር ጭምር ከልማትና ዕድገቷ ስትጎትታት መቆየቷ የሺህ ዘመናት የአደባባይ ሐቅ ነው።
በዚህ ታሪካዊ ሸፍጥ ቁጭት የገባቸው ኢትዮጵያውያንም ከዓድዋ ጀግኖች የተረከቡትን የጀግንነት ወኔ በመላበስ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በጉባ ተራሮች ግርጌ ዓባይን በማቀብ ብርሃንን ፈንጥቀዋል።
ይህም ዓባይ “ግንድ ይዞ ይዞራል” የተባለለትን የዘመናት ተረትም በመቀየር ሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው ብርሃን ከሀገር የተሻገረ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል በመፍጠር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ በረከትን ፈጥሯል።
በሕዳሴ ግድብ የተፈጠረው ቀጣናዊ የኃይል ትስስርም የኢትዮጵያን በጋራ የማደግ ቀጣናዊና አፍሪካዊ ራዕይን በአደባባይ የገለጠ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ትልም ሆኖ ተመዝግቧል።
የውሃ ሃብት ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታራምደው የሺህ ዘመናት ወንዙን በብቸኝነት የመጠቀም ግትር አቋም ከራስ ወዳድነት የሚመነጭ ስሁት ትርክት ነው።
የሕዳሴ ግድብም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን የደለል ክምችት፣ የጎርፍና የድርቅ አደጋ በመቀነስ እንዲሁም የሀገር ውስጥና ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት ትስስርን በማጠናከር ዘርፈ ብዙ በረከትእያስገኘ ነው ብለዋል።
ግብፅ የዓባይን በብቸኝነት የመጠቀም ስግብግብ ፍላጎቷ የሺህ ዘመናት ትርክት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅትም የግብፅ የፖለቲካ ልሂቃን በቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች በመቸንከር ዓባይን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎትና ሕዳሴ ግድብ ላይ ስሁት ትርክታቸውን በመንዛት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም ሕዝቦቿን በማስተባበር በዓለም አቀፍ ሕግና መርህ በሳይንሳዊ መንገድ ሕዳሴ ግድብን በመገንባት ፍትሐዊ የድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብት ተጠቃሚነትን በተግባር ማስመስከሯን አስረድተዋል።
ግብፅ ለዓባይ ወንዝ የውኃ ምንጭ ምንም ዓይነት አበርክቶ የላትም ያሉት ተመራማሪው፤ ለሺህ ዘመናት ለብቻየ ልጠቀም የሚለው እሳቤም ኢ-ፍትሐዊ ከመሆኑም ባሻገር መሠረተ ቢስ ፍላጎት ነው ብለዋል።
የተፋሰሱን ሀገራት የዓባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት ድርድርና ስምምነቶች በማስተጓጎልም የተሳሳተ አማራጭን እየተከተለች እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም እስካሁን የውኃ ሀብቶቿን የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራትና ጎረቤቶቿን በማይጎዳ መንገድ ማልማቷን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አስገንዝበዋል።
ግብፅ በሕዳሴ ግድብና በዓባይ ወንዝ ላይ የምታስተጋባው የተሳሳተ መረጃም መሠረተ ቢስ ክስና ማረጋገጫ የሌለው የሺህ ዘመናት ስሁት ትርክት ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።
ሕዳሴ ግድብና ሌሎች የኃይል ማመንጫ ግድቦች የኢትዮጵያን የውኃ ልማት ዕውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሯል ብለዋል።
በቀጣይም በዓለም አቀፍ ሕግና መርህ በመመስረት በዓባይና ሌሎች የውኃ ሀብቶች ላይ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግናን የሚያረጋግጥ የልማት ሥራን ማስቀጠል እንዳለባት ገልጸዋል።