ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገራት ከቀረበው የኃይል ሽያጭ 475 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች-ኢንጂነር አሸብር ባልቻ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገራት ከቀረበው የኃይል ሽያጭ 475 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች-ኢንጂነር አሸብር ባልቻ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22 /2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገራት ከቀረበው የኃይል ሽያጭ 475 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አስታወቁ።
ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ካለፈው በጀት ዓመት በ23 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ የማመንጨት አቅሙ 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት መድረሱን አስታውቀዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ የ124 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ በማስገኘት የ39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማስመዝገብ እንደቻለ አስታውቀዋል።
የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የተሳካው አጠቃላይ የእቅዱ 101 ነጥብ 83 ከመቶ አፈጻጸም በተቋሙ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ የትርፍ አፈጻጸም ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
ለውጭ ሀገራት ከቀረበው የኃይል ሽያጭም 475 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ25 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ከተመረተው የኤሌክትሪክ ኃይልም የውኃ ማመንጫዎች 97 በመቶ ድርሻ መያዙን ገልጸዋል።
በቀጣይም የገናሌ ዳዋ 6 የውኃ ኃይል ማመንጫ፣ የአይሻ 2ኛ የንፋስ ኃይል ማመንጫና በሀገር ውስጥ ፋይናንስ የሚገነባ የ100 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር እቅድ መያዙን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ 40 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።