የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከብክለት የጸዳ ከባቢና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር አስተዋጽኦ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከብክለት የጸዳ ከባቢና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር አስተዋጽኦ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከብክለት የጸዳ ከባቢና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የግሎባል ፈንድ የአፍሪካ ተወካዮች ቢሮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሄንሪ ፎሙንዳም ገለጹ።
በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 76ኛው የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል።
የአፍሪካ ሀገራት፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የጤና መሪዎች በተሳተፉበት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ዲጂታልና ሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘ የጤና ሥርዓት ግንባታ በሽታን በመከላከልና አክሞ በማዳን አቅም ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆን ጥረት እያደረገች መሆኑ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከ50 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለግብርና ምርታማነት፣ ለመድኃኒት ቅመማና ለአየር ንብረት ደኅንነት ውጤት እያስመዘገበች መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት ዶክተር ሄንሪ ፎሙንዳም ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአፍሪካ ጠንካራና ዘላቂ ዋስትና ያለው የጤና ሥርዓት ለመገንባት ትብብር ወሳኝ ነው።
የአፍሪካውያን ዕውቀት፣ የተፈጥሮ ጸጋና በቂ የሰው ኃይል የጤና ፋይናንስና የአስተዳደር ሥርዓቱን በማዘመን የራሳቸውን ጠንካራ የጤና ተቋማት መፍጠር እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን በመቀነስ የዜጎችን በሕይወት የመኖር ምጣኔ እንደሚያሻሽል ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አፍሪካዊት ቀዳሚ ሀገር በመሆን ከብክለት የጸዳ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካውያን የጤና ሥርዓታቸውን በራሳቸው አቅም ለመገንባት ከአጋር አካላት ጋር የሚኖራቸው ትብብር በትይዩ እንጂ ሰጪና ተቀባይ እንዲሆን መፍቀድ እንደማይገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ከጤና የተሻገረ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ራስን መቻል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአህጉሪቷ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ትስስር ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።