ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የቱሪስት ፍሰትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የዘርፉ ገቢ እንዲጨምር አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የቱሪስቶችን ፍሰት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የዘርፉን የገቢ ምንጭነት እያሳደጉት መምጣታቸውን የክልሉ ደንና የዱር እንስሳት ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ደንና የዱር እንስሳት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አራርሳ ረጋሳ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የደን ሃብትን በማልማት ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ትኩረት ከመስጠት ባሻገር የቱሪዝም መስህብና የሀብት ምንጭ ማድረግ ስለመቻሉ አንስተዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የደን ሽፋን በማደጉ የዱር እንስሳት ደህንነት እንዲጠበቅና ሸሽተው የነበሩም እንዲመለሱና ይበልጥ እንዲበራከቱ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በዚህም የዱር እንስሳትና ብርቅዬ አእዋፋት ጭምር ሁነኛ የጎብኝዎች መስህብ እየሆኑ በመምጣታቸው አበረታች ገቢ እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘርፉ ልማት የስነ-ምህዳር መታደስን ከመፍጠሩ በላይ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ትኩረት መሳብ ያስቻለ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በክልሉ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮችን ተፈጥሮአዊ ሀብት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ሕጋዊ የአደን ስፍራዎችን በመለየት የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

በእርጅና ላይ የሚገኙና ጉዳት የደረሰባቸውን የዱር እንስሳት በመለየትም እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም