ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ተደርጓል

ሚዛን አማን፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ለ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ተግባር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለሙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በትምህርት ቤቶች ተከናውነዋል።

በትምህርት ቤቶቹ የተማሪ መማሪያ ክፍሎችን ምቹ የማድረግ፣ የመጽሐፍት አቅርቦት የማሟላት እና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በ2018 ዓ.ም ብቻ 46 አዳዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ተገንብተው ለመማር ማስተማር ዝግጁ መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ992 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለማስተማር ታቅዶ የምዝገባ ሂደት በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ምዝገባው በ1 ሺህ 568 የአንደኛ ደረጃ እና በ186 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ ነው።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሙሉቀን አበበ፤ ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን 3 ሺህ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም የግቢ ውበት ማስጠበቅ፣ የተማሪ ወንበር እድሳት፣ ቤተ መጽሐፍትን ማደራጀት እና ሌሎች ለመማር ማስተማሩ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ከ30 በመቶ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ወላጆች ያልተመዘገቡ ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡም ጥሪ አቅርበዋል።

ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ ካገኘናቸው ወላጆች መካከል አቶ ሀብታሙ አስፋው፤ "ልጄን በአግባቡ የማስተማር ግዴታዬን ለመወጣት በወቅቱ አምጥቼ አስመዝግቤያለሁ" ብለዋል።

ከማስመዝገብ ባሻገር መደበኛ ትምህርት ሲጀመር ከትምህርት ቤቱ ጋር በቅርበት በመገናኘት ለልጃቸው ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ነገ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችላትን እውቀት ለመቅሰም በራስ ተነሳሽነት መመዝገቧን የተናገረችው ደግሞ ተማሪ ምህረት ክፍሌ ናት።

እንደርሷ ሁሉ በጎረቤቷ ያሉ ሌሎች ተማሪዎችም ወደ የትምህርት ቤቶቻቸው በመሄድ እንዲመዘገቡ የምታበረታታ መሆኑን ተናግራለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም