የኢትዮጵያን ድል ያበሰረ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ድል ያበሰረ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ድል ያበሰረ፣ ሕብረ ብሔራዊነትን የጠበቀ፣ አካታችና አሳታፊ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን በጉባኤው የተሳተፉ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ተወካዮች ገለጹ።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአርባ ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ተጠናቅቋል።
በእንግሊዝ እና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ አካታችና ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነጻነት አንጸባርቀውበታል።
በእንግሊዝ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪ ኡስታዝ ሙክታር ጀማል እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገርን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረና ኢትዮጵያ አሸናፊ የሆነችበት መድረክ ነው።
ምክክሩ ዳያስፖራውን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተወካይ አማካኝነት የተሳተፈበት ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነፃነት ያንፀባረቁበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪ ገዛኸኝ ሱማሞ በበኩላቸው፤ ምክክሩ የመነጋገር ባህልን የሚያዳብርና ሀገራዊ ድምፆች የተንፀባረቁበት ታሪካዊ መድረክ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ብዝሃነት የተንፀባረቀበትና ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማሻገር የሚያስችል ውጤታማ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላም፣ የጋራ መግባባትና ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተዋፅኦ ያለው ጉባዔ መሆኑንም ገልጽዋል።
ዳያስፖራው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ልምዱን ለማካፈል ወርቃማ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል።