ቀጥታ፡

ለትውልድ የሚተርፍ ውርስ፡የአረንጓዴ አሻራ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ

ድርቅ እና የደን መጨፍጨፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለበርካታ ዓመታት ሲነሱ የቆዩ ጉዳዮች ናቸው።

ኢትዮጵያ ይሄን ታሪኳን ለመቀየር ቆርጣ ከተነሳች ዓመታት ተቆጥረዋል።አረንጓዴ አሻራ-ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በአካባቢ ጥበቃ እና የማይበገር የአየር ንብረት ለውጥ አቅም ግንባታ ግንባር ቀደም የሆነ የለውጥ ሞተር ሆኗል።

በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ብዝሃ ህይወትን ወደ ቀደመው ስፍራ ለመመለስ፣በረሃማነት ለመከላከል፣የደን ሽፋንን ከመጨመር አልፎ የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ጥረቶች አስተዋጽኦ እስከ ማበርከት ደርሷል።

የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች እና ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ጋር በመሰናሰል ዘላቂ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት ትልም አለው።

ኢኒሼቲቩ ድንበር ተሻጋሪ ተጽእኖ ያለው ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም።አረንጓዴ አሻራ በደን መልሶ ማልማት አማካኝነት ዛፎችን ወደ ይዞታቸው በመመለስ ወደ አየር ሊለቀቅ የሚችል በሚሊዮን ቶኖች የሚቆጠር ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ አምቆ በመያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካርቦንዳይ ኦክሳይድን ከከባቢ አየር የማስወገድ እና የማከማቸት ጥረት ውስጥ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የካርቦን ዳይኦክሳይድን አምቆ መያዝ እና ማከማቸት በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።

ድንበር ተሻጋሪው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአፍሪካ ቀንድ የመሬት መሸርሸርን ከመከላከል፣የደን ሽፋንን በመጨመር፣በረሃማነትን ከመከላከል እንዲሁም በአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የራሱን በጎ ሚና ተጫውቷል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አየር ንብረት ለውጥ ውይይቶች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሯ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመቀነስ ረገድ እያበረከተ ያለው ሚና እውቅና የተሰጠው ነው።

መልከ ብዙው አረንጓዴ አሻራ በአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አዲስ አማራጭን ይዞ የመጣ እንደሆነም ይነገርለታል።

ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና አካባቢ ጥበቃ ስራ የውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ ከመሆን በሀገር ውስጥ አቅም ሀብት የማሰባሰብ ሞዴል መፍጠር ችሏል።

ሀገር በቀል ፋይናንስ፣የማህበረሰብ ጉልበት እና የአይነት ድጋፎች ተዳምረው በአነስተኛ በጀት ፈጠራ የታከለበት የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ ማከናወን እንደሚቻል አሳይቷል።

ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አየር ንብረት ለውጥ ፈንድ (GCF)፣ የዓለም ባንክ፣የተባበሩት መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮግራም እና ሌሎች አጋሮች ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የገንዘብ ድጋፍ እና የቴክኒክ ድጋፎችን አግኝታለች።

የተገኘው ዓለም አቀፍ ድጋፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲዎች የበለጠ እንዲተሳሰሩ አድርጓል።

አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦችን ከኢኮኖሚ ልማት፣ ስራ ፈጠራ፣ አረንጓዴ ቱሪዝም እና ዘላቂ ግብርና ጋር በማስተሳሰር ሁሉን አቀፍ እይታን መፍጠር ጥሏል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሀገሪቷ የደን ሽፋን መጨምርም ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት የነበረው የሀገሪቱ የደን ሽፋን 17 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን ባለፈው አመት በተጠናው ጥናት ሽፋኑ 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

አረንጓዴ አሻራ ከ20 ዓመት በፊት ከአራት በመቶ በታች የነበረውን የኢትዮጵያን የደን ሽፋን መልሶ እንዲያንሰራራ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የተራቆቱ አካባቢዎችን በፍጥነት ተንከባክቦ ማዳንና ምርታማ በማድረግ፣ የተራቆተ መሬትን በእጽዋት የማልበስ ስራ ላይ ጉልህ አበርክቶ አለው።

አረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የደኖች ብዝሃ ህይወት ዳግም እንዲያብብና የማይበገር የአየር ንብረት ለውጥ አቅም ግንባታ ላይ የድርሻውን ተወጥቷል።

በአረንጓዴ አሻራ ለደን እና ለውበት ከሚተከሉት ችግኞች ባሻገር በጥምር ደን እርሻ ለፍራፍሬ እና መኖ የሚውሉ ምግቦች በብዛት በማምረት የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል።

ሲጠቃለል አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከል ዘመቻ ያለፈ ነው።የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል፣ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን የመፍጠር ትልቅ ለውጥ ያለው ኢኒሼቲቭ ነው።

በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የአየር ንብረት ግቦች እንዲሳኩ በፖለቲካ ቁርጠኝነት፣በማህበረሰብ ተሳትፎ፣ በፈጠራ መፍትሄዎች እና ሁሉን አቀፍ ተግባራት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉም የሚያመላክት ተምሳሌታዊ ኢኒሼቲቭ እንደሆነም ሊሰመርበት ይገባል።

ዓለም በአየር ንብረት ስጋቶች ውስጥ እየኳተነች ባለችበት ወቅት የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ልምድ የተስፋ ጮራ የሆነና አረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል በተግባር አሳይቷል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በተፈጥሮ ላይ እየሰራች ለትውልድ መጻኢ ጊዜን እየጠበቀች ነው።ይህ ተግባር ከሀገር አልፎ ድንበርን ተሻግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም