የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ድልድል ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ድልድል ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21 /2018(ኢዜአ)፦ የ2026/27 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ድልድል ዛሬ ማምሻውን በሞናኮ ይፋ ሆኗል።
ውድድሩ ጳጉሜን 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይጀመራል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከ2016 ዓ.ም የውድድር ዓመት አንስቶ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ፎርማትን በማስቀረት 36 ክለቦች በ4 ቋቶች (Pots) በመከፋፈል እንዲጫወቱ የሚያደርግ አዲስ አሰራር (League Phase) መተግበር መጀመሩ ይታወቃል።
በዚሁ መሰረት 36ቱ ቡድኖች በ4 ቋቶች የተደለደሉ ሲሆን በእያንዳንዱ ቋት 9 ክለቦች ይገኛሉ።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ፣ ሪያል ማድሪድ፣ ባየር ሙኒክ፣ ማንችስተር ሲቲ፣ አርሰናል፣ ባርሴሎና፣ ኢንተር ሚላን፣ ሊቨርፑል እና አትሌቲኮ ማድሪድ ተደልድለዋል።
ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ፣ ሮማ ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን ፣ አስቶንቪላ፣ ፓርቶ፣ ማንችስተር ዩናይትድ ፣ ክለብ ብሩዥ፣ ሪያል ቤቲስ እና ፒኤስጂ አይንድሆቨን በቋት ሁለት የሚገኙ ክለቦች ናቸው።
በቋት ሶስት ላይፕዚግ፣ ቪያሪያል፣ ናፖሊ፣ ሊል፣ ፌይኖርድ ሮተርዳም፣ ቦዲ ግሊምት፣ ፊነርባቼ፣ ሻካታር ዶኔስክ እና ጋላታሳራይ ላይ ይገኛሉ።
ስቱትጋርት፣ ሌንስ፣ ስላቪያ ፕራግ፣ ስሎቫን ብራቲስላቫ ፣ ኤኢኬ አቴንስ ፣ ላስክ፣ ኮሞ፣ ቫይኪንግ እና ሳባህ በቋት አራት የተደለደሉ ክለቦች ናቸው።
አንድ ክለብ በራሱ ቋት ካለ ሁለት ቡድንና በእያንዳንዱ ቋት ካሉ ሁለት ክለቦች ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
በዚህም አንድ ክለብ ስምንት ጨዋታ ያደርጋል።
ከ36 ክለቦች መካከል በስምንት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ይገባሉ።
ቀሪዎቹ ስምንት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ ቡድኖች በሁለት የማጣሪያ ዙሮች ተጫውተው 16ት ውስጥ ይገባሉ።
ከጥሎ ማለፉ አንስቶ ያለው የውድድር ፎርማት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።
በዚሁ መሰረት ሪያል ማድሪድ ከአርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ ከባርሴሎና፣ ማንቸስተር ዩናይትድ ከባየር ሙኒክ ፣ ባርሴሎና ከፒኤስጂ እና ሊቨርፑል ከአትሌቲኮ ማድሪድ በመጀመሪያው ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል የሚጠበቁ ናቸው።
የጣልያኑ ኮሞ እና የአዘርባጃኑ ሳባህ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው።