የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት አግዞናል -በሃዋሳ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት አግዞናል -በሃዋሳ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች
ሀዋሳ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዳገዛቸው በሃዋሳ ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡
የመደመር መንግስት እሳቤ የሆነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በርስ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ይገኛል፡፡
በሃዋሳ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ፤ ዓመታትን የተሻገሩ ችግሮቻቸውን በመፍታት በተስፋ እንዲኖሩ እንዳስቻላቸው ለኢዜአ ገልፀዋል።
በከተማው የፋራ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ አማረች አበራ በእርጅና ያዘመመ ቤታቸው በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና በመንግስት ትብብር በአዲስ መልክ መሰራቱ ህይወታቸውን በተሻለ መንገድ ለመጀመር እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡
በበጎ ፈቃዱ ያረጀ ቤታቸው ብቻ ሳይሆን ጉስቁልና የተጫጫነው ኑሯቸው እንዲቀየር የወገን አለኝታነት ከፍተኛ እገዛ እንዳረገላቸው ነው ያመለከቱት።፡
የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው ቤት በመቀመጣቸው ለገጠማቸው ችግር በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መፍትሄ ማግኘታቸውን የጠቀሱት ደግሞ የሂጠታ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሹቃ ፋሬሾ ናቸው።
የበጎ ፈቃድ የመደጋገፍ ባህል እያደገ መምጣቱ እሳቸውን መሰል በእድሜ የገፉና በህመም ምክንያት መንቀሳቀስ ያልቻሉ ዜጎችን ለማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ2011 ጀምሮ በመሳተፍ ላይ መሆኑን የገለጸው ወጣት ተመስገን ያዕቆብ፤ አቅሙን፣ ጉልበቱንና ጊዜውን አስተባብሮ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን እያገዘ ይገኛል።
በዚህም በገንዘብ የማይተመን የመንፈስ እርካታ ከማግኘት ባለፈ አገርና ህዝብን በማገዝ የዜግነት ግዴታውን እየተወጣ መሆኑንም ይናገራል።
የታቦር ክፍለ ከተማ ወጣቶች ክንፍ አስተባባሪ ወጣት መልካሙ ሚካኤል በበኩሉ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በክረምትና በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሳተፉ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይናገራል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የወጣቶችን ስብዕና በመገንባት አገራዊ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ነው የገለጸው።
የሃዋሳ ከተማ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት ወልደጻዲቅ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ90 ሺህ በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል ብለዋል።
በዚህም 246 ሚሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት ለመስጠት ግብ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በ18 ዘርፎች የሚከናወን ሲሆን፤ የቤት እድሳትና ግንባታ፣ የማዕድ ማጋራት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የደም ልገሳና ሌሎችንም ተግባራት የሚያካትት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ99 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡