ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ቀጣናዊ ትብብርና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለመ የሕልውና ጥያቄ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ቀጣናዊ ትብብርና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጠ ያለመ ፍትሐዊና የሕልውና ጥያቄ መሆኑን በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ገለጹ።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የባሕር በር ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለቀጣናዊና ዓለም አቀፍ የንግድ ትብብር ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው የህልውና ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የሕዝብ ቁጥር ታሳቢ በማድረግም ሀገርን ከታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ መልክዓምድራዊና ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነቷ ማስታረቅ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም ብለዋል።

ስትራቴጂክ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም በትብብር ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ የጋራ ዕድገትና ብልፅግናን የሚያሳልጥ የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ጥናቶች መሠረት ወደብ አልባ ሀገራት ከባሕር በር ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት ጋር ሲነጻጸሩ እስከ 25 በመቶ የሚደርስ የአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ልዩነት እንደሚያጋጥማቸው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነው ገቢና ወጪ ንግድ በአንድ ወደብ በኩል መከናወኑም ለሌሎች የልማት ሥራዎች ይውል የነበረው የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስወጣ ተናግረዋል።

ይህም በዓለም ንግድ ሥርዓት የወጪና ገቢ ተወዳዳሪነትን በማቀጨጭ በኢንዱስትሪ፣ ኢንቨስትመንትና በዜጎች ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ታሪካዊ መሠረትም ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ለሺህ ዓመታት በአዱሊስ ወደብ አማካኝነት ከዓለም ጋር ሰፊ ግንኙነት ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር አቅራቢያ የተፈጠረች ሀገር መሆኗ በተፈጥሯዊና መልክዓምድራዊ አመክንዮ የተደገፈ ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግጋትና የኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት ኢ-ሕጋዊ መንገድም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ ሕጋዊ መሠረት እንዳለው አስረጂ መሆኑን አብራርተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነትና ሕግጋትም ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስና የመጠቀም መብታቸውን የሚደግፍ ድንጋጌና ማዕቀፍ መኖራቸውን አንስተዋል።

አክለውም በቅርቡ በቱርክሜኒስታን አዋዛ ከተማ በተካሄደው የወደብ አልባ ታዳጊ ሀገራት ጉባኤ፣ በዚህ ዘርፍ ጉልህ ውሳኔዎች መወሰናቸውን ጠቁመው፣ የአዋዛ የፖለቲካ መግለጫም መጽደቁን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎትም የግል ጥቅምን ብቻ ለማሳካት የቀረበ ሳይሆን የጋራ ቀጣናዊ ህልውናን በማስጠበቅ ትብብርንና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያም ይህንን አቋም ለጎረቤት ሀገራት በሁለትዮሽ እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እያስረዳች መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም