ቀጥታ፡

ምክክሩ ኢትዮጵያውያን አለመግባባቶችን በሐሳብ የበላይነት መፍትሔ መስጠት እንደሚችሉ በተግባር የታየበት ነው

ወልቂጤ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን አለመግባባቶችን በሐሳብ የበላይነትና በጥበብ መፍትሔ መስጠት እንደሚችሉ በተግባር የታየበት መሆኑን የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን በመግባባት ዘላቂ ሰላምን እውን ማድረግ የሚችሉት በኃይል አማራጭ ሳይሆን የሐሳብ የበላይነትን ባስቀደመ አካታች ውይይት ብቻ መሆኑን በተግባር ያሳየ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ነው።

ተመካካሪዎቹ ልዩነቶቻቸውን በግልጽነት አቅርበው በጥበብና በመደማመጥ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት፣ የሚነሱ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍትሔ የመስጠት ልማድ እንዲዳብር መሠረትን ይጥላል።

ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን አለመግባባቶችን በሐሳብ የበላይነት መፍትሔ መስጠት እንደሚችሉ በተግባር የታየበት ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ጥሩነሽ ምኑታ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ የመመካከርና የመወያየት ባህላቸውን በመጠቀም ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ ጉባኤው ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ እስክንድር ነጋሽ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን በራሳችን ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ መፍትሔ መስጠት እንደምንችል ያስገነዘበ እንደሆነም አንስተዋል።

የምክክር ጉባኤው በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ፣ በጠንካራ ሀገረ መንግሥት የጸናች ሃገርን በመገንባት ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል መርህ የተከተለ እንደነበረም ጠቅሰዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በራሳችን አቅምና በጋራ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ታሪካዊ ዕድልን የፈጠረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ዳዊት ብርሃኔ ናቸው።

ምክክሩ ቀጣይነት ያለው ሰላም፣ አንድነቱ የተጠበቀና በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባ ሀገርን ለማንበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም አመልክተዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ እኩል እንዲመክርና እንዲወከል በማድረጉ ሀገራዊ ስሜትን ያነቃቃና ባለቤትነትን ያረጋገጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ሃዲሞ ሃሰን ናቸው።

ምክክሩ በሕዝቦች መካከል ያሉ የጋራ እሴቶችን በማጠናከር ረገድ ወደ ተሻለ አንድነት የሚያመጣ መሆኑን አውስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም