ቀጥታ፡

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባዔ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶችን በተሞክሮነት ያቀረበችበት ኹነት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባዔ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶችን በተሞክሮነት ያቀረበችበት ስኬታማ ሁነት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባዔ በስኬት ተጠናቋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ለኢዜአ እንዳሉት፤ 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባዔ የኢትዮጵያ ውብ ገፅታ የተገለጠበት መድረክ ነው።

ኢትዮጵያ በሽታን ለመከላከልና አክሞ ለማዳን የሚያስችል የጤና ፖሊሲ በመቅረፅ በዜጎች ጤና ላይ መሰረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች ብለዋል።

የእናቶችና ህፃናትን ሞት በመቀነስ፣ በመከታተል በቴክኖሎጂ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈ የጤና ስርዓት በመገንባት እመርታ መምጣቱን ገልጸዋል።

በጉባዔው ኢትዮጵያ የ76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባዔ ሊቀ-መንበር ሆና መመረጧን አስታውሰው፤ በጤናው ዘርፍ በዓለም መድረክ አፍሪካን ወክላ ንቁ ተሳትፎ ታደርጋለች ብለዋል።

ጉባዔው ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ልምዷን ያካፈለችበት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠችበት መሆኑንም ገልጸዋል።

አፍሪካ የራሷን የጤና ፋይናንስ አቅም በራሷ መሸፈን መቻል እንዳለባት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የመድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በስፋት ማምረት መጀመሯን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን ጋር በትብብር የማደግ ግቧን ለማሳካት ልምዷን አካፍላለች፤ ከሌሎችም ትማራለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም