በመዲናዋ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የደንብ ማስከበር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የደንብ ማስከበር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦በመዲናዋ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የደንብ ማስከበር እና ጥሰቶችን የመከላከል እንዲሁም የመቆጣጠር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጸጸምና የ2019 በጀት ዓመት እቅዶች ላይ ከህዝብ ተወካዮች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከ1200 በላይ የከተማው ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደገለጹት ተቋሙ በ2018 በጀት አመት አፈጻጻም የላቀ ውጤት በማምጣት ተሸላሚ መሆኑን ገልጸው ይህ ስኬት የተገኘው ከከተማው ነዋሪዎች በጋራ በመስራት ነው።
ባለፈው በጀት ዓመት በተቋም ግንባታ፣ ምቹ የስራ ከባቢን ከመፍጠርና የባለሙያዎችን አቅም ከመገንባት አንጻር ወጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት በቴክኖሎጂ የሚመራ ተቋም መገንባት የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውንም ነው የተናገሩት።
ዲጂታል የጥሪ ማእከል፣ ስማርት ኦፊስ፣ በሲሲቲቪ ካሜራ እና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት የከተማዋን ሰላም የሚያጠናክሩ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ መዋላቸውን ጠቅሰዋል።
የደንብ ጥሰትን መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ላይም ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውን አንስተዋል።
የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት የመገንባት፣ የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በስፋት መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ሻምበል በለጠ ጭናሾ እና አቶ ታረቀኝ ደሳለኝ የደንብ ማስከበር ስራዎች በአዲስ አበባ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን ከጉዳት ከመጠበቅ አኳያ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን አንስተዋል።
የደንብ ጥሰቶችን በመከላከልና መሰረተ ልማቶችን በባለቤትነት ስሜት በመጠበቅ በኩል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።