ግብፅ ለኢትዮጵያ ተገቢውን ዋጋ መክፈል አለባት-አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ ለኢትዮጵያ ተገቢውን ዋጋ መክፈል አለባት-አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ለምታበረክተው የ86 በመቶ የውሃ ሀብት ድርሻ ግብፅ ተገቢውን ዋጋ መክፈል እንዳለባት የቀድሞ የውሃ ሀብት ሚኒስትር አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በዓባይና በሌሎች ታላላቅ ወንዞቿ ላይ የመስኖ ግድብ በመገንባት ሁለንተናዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የግብርና ምርታማነትን ማፋጠን እንዳለባትም አምባሳደር ሽፈራው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿ የዘመናት ዕዳዎቿ እስኪመስሏት ድረስ ግብፅ በሸረበችው ሴራ አማካኝነት ሳትጠቀም ብትቆይም፤ ኢትዮጵያዊያን የተሸረበባቸውን ሴራ በመበጠስ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገንባት ብርሃን በመፈንጠቅ አንድነታቸውን አሳይተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ከሀገር በመሻገር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ በረከት ለመፍጠር ተችሏል።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የተፈጠረው ቀጣናዊ የኃይል ትስስርም የኢትዮጵያን በጋራ የማደግ አፍሪካዊ ርዕይን በአደባባይ የገለጠ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ትልም ሆኖ ተመዝግቧል።
የኢትዮጵያ የቀድሞ የውሃ ሀብት ሚኒስትር አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ግብፅ ለረጅም ዘመናት በምትከተለው ዓባይን የመቆጣጠር ፖሊሲ ምክንያት ኢትዮጵያ ዓባይን ሳትጠቀም ቆይታለች።
ለረጅም ዘመናት ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የጠላትነት ትርክት ስታራምድ መቆየቷን ጠቁመው፤ በዚህም ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ በማልማት ሳትጠቀም ዓመታትን ማሳለፏን ተናግረዋል።
በዚህ ቁጭት ኢትዮጵያውያን በሕብረ ብሔራዊ አንድነት በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ግዙፉን ዓለም አቀፍ የኃይል ማመንጫ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን እውን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የመፈጸም አቅም በዓለም መድረክ ያሳየ ታሪካዊ የትውልድ አሻራ መሆኑን አውስተው፤ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት አስተማማኝ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ በማድረግ የጎርፍ አደጋንና የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ትልቅ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ሌሎች የቀጣናው ሀገራት ጋር የፈጠረችው የኃይል ትስስርም ቀጣናዊና አህጉራዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማፋጠን ጉልህ ፋይዳ እያበረከተም መሆኑን ገልጸዋል።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረው ቀጣናዊ የኃይል ትስስርም ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጫፍ እስከ አውሮፓ አባል ሀገራት የሚሻገር የኃይል ትስስር የማጠናከር አቅም እንዳላት ማሳያ ነው ብለዋል።
የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት የአንድን ሀገር ልማትና ዕድገት ከማሳለጥ ባሻገር በትብብር የማደግ ርዕይን የሚያሳካ ወሳኝ መሠረተ ልማት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያን በታሪካዊ ጠላትነት የምትመለከትበት የግብፅ የትርክት ሴራ በአንድ በኩል የውሃ ጉዳይን ከፖለቲካ ጋር እንዲቆራኝ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው የትብብር ሂደት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።
በትብብር መንፈስ መሥራት ከተቻለ ኢትዮጵያ በግድቦቿ የምታከማቸውን የውሃ መጠን በመቆጣጠር የጎርፍ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባሻገር በድርቅ ወቅት የሚጠቅም የውሃ አስተዳደር ሥርዓት ማስፋፋት እንደሚቻል ነው ያመለከቱት።
ሀገራት በፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመሥርተው አብረው ማደግ አለባቸው ያሉት አምባሳደሩ፤ ለዚህም ግብፅ ከግጭትና ከጠላትነት ትርክት በመውጣት የትብብር መንፈስን መከተል እንዳለባት አስገንዝበዋል።
ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ከምታራምደው የብቻ የተጠቃሚነት ፍላጎትና አቀራረብ በመላቀቅ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ሀብታቸውን በፍትሐዊና ምክንያታዊ መንገድ እንዲጠቀሙ በትብብር መሥራት እንዳለባት ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ለምታበረክተው የ86 በመቶ የውሃ ሀብት ድርሻ ግብፅ ተገቢውን ዋጋ መክፈል እንደሚጠበቅባትም ነው የተናገሩት።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ዓባይ ወንዝን ጨምሮ በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿ ላይ ተጨማሪ ግድቦችን በመገንባት የኃይልና የመስኖ አቅሟን ማሳደግ እንዳለባት አምባሳደር ሽፈራው አስገንዝበዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የኃይል ማመንጫ ግድቦችንና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችላትን የሰው ኃይል፣ የገንዘብ አቅም፣ ልምድና ተሞክሮ ለማዳበር አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
በዚህም የግብርና ምርታማነትን የበለጠ ለማሻሻል በዓባይና በሌሎች የውሃ ሀብት ወንዞቿ ላይ የመስኖ ልማትን በስፋት በማከናወን የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡ ግድቦችን መገንባት እንደሚኖርባት አብራርተዋል።
በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል የውሃ ሀብትን በፍትሐዊና ምክንያታዊ መንገድ መጠቀም፣ መጠበቅና በትብብር ማልማትን ያለመው የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የጋራ የውሃ አስተዳደር ሥርዓትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የናይል ትብብር ማዕቀፉን ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን የፈረሙት ሲሆን፤ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን ደጋግመው የሚያነሱት ግብፅና ሱዳን ግን ማዕቀፉን እስካሁን አልፈረሙትም።
አምባሳደር ሽፈራው እንደሚሉት፤ ግብፅና ሱዳን የናይል የትብብር ማዕቀፉን አለመፈረማቸው በቅኝ ግዛት ዘመን በብቸኝነት የመጠቀም ኢ-ፍትሐዊ አካሄድን ለማስቀጠል ከሚመነጭ ለብቻ የመጠቀም ፍላጎት ነው።
በአሁኑ ወቅትም ግብፅ የናይል የጋራ ትብብር ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ እያለ በራሷ መንገድ ትብብር ለመፍጠር ጥረት የምታደርገው ፍትሐዊ የውሃ ሀብት የጋራ ተጠቃሚነትን የማትቀበል መሆኗን በገሃድ የሚገልጥ የአደባባይ ሐቅ ነው ብለዋል።