በሲዳማ ክልል ከተሞችን ይበልጥ በማዘመን ለስራና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ከተሞችን ይበልጥ በማዘመን ለስራና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤ ነሀሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ከተሞችን ይበልጥ በማዘመን ለስራና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች በሀዋሳ፣ ይርጋለም፣ አለታ ጩኮና አለታ ወንዶ ከተሞች እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር፣ የሀይቅ ዳርቻ ልማት፣ የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት፣የትምህርትና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች የላቀ ስኬት እየተመዘገበባቸው ይገኛል ብለዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን ለስራ፣ ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ እና መልካም አስተዳደር የሰፈነባቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛል።
የሀዋሳ ኮሪደር ልማት አራተኛውን ዙር ለአገልግሎት ማብቃት እንደተቻለ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በይርጋለም፣ አለታ ወንዶ፣ ወንዶገነት፣ ዳዬና ለኩ ከተሞችም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀዋሳ ከኮሪደር ልማቱ ጎን ለጎን የሀይቅ ዳርቻ ልማት ስራ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን አንስተው በተያዘለት ጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ሌት ከቀን ያለምንም እረፍት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሲዳማ ክልል ሀዋሳን ጨምሮ ሌሎች ከተሞችንም ይበልጥ በማዘመን ለስራና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ስድስት ከተሞች የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው የሲዳማና የሀዋሳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ወደ ስራ በመግባት ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደርና የሀይቅ ዳርቻ ልማት ስራዎች ሀዋሳን በአፍሪካ ተመራጭ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል መሰረት የተጣለባቸው ናቸው ብለዋል።
አራተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ጠቁመው የሀይቅ ዳርቻ ልማቱንም በታቀደለት ጊዜ በጥራት ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሰባቱንም ቀን ለ24 ሰዓት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው በክልሉ የትምህርት ስብራትን በመጠገን የተሟላ ዕውቀትና ስብዕና የተላበሰ ዜጋን ለማፍራት በሚያስችል መልኩ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በፌዴራል፣ በክልሉ መንግስት፣ በማህበረሰቡና አጋዥ ድርጅቶች የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
እየተገነቡ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በትምህርት ሚኒስቴር እየተገነባ ያለውና በአለታ ጩኮ ከተማ የሚገኘው የሩፎ ዋኢኖ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2019 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጁ መደረጉን ገልጸዋል።
የደቡባዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ ፊታሞ እንዳሉት በዞኑ የኮሪደር ልማትን ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል።
በዞኑ አለታ ወንዶን ጨምሮ በሶስት ከተሞች የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ያካተተ የኮሪደር ልማት እየተካሄደ እንደሚገኝና የአለታ ወንዶ ከተማን በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የዞኖች፣ የወረዳና የከተሞቹ አመራሮች ተገኝተዋል።