ቀጥታ፡

በከተማው ተግባራዊ የተደረገው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለልማትና መልካም አስተዳደር ስኬቶች አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል

ደብረ ብርሃን፤  ነሀሴ 21/2018 (ኢዜአ)፡-  በደብረ ብርሃን ከተማ ተግባራዊ የተደረገው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለልማትና መልካም አስተዳደር ስኬቶች አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የተቋማት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ የውይይት መድረክ አካሄዷል።


 

በመድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብእሸት እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል። 

በተለይም በሰላም ማስፈን፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ኢንቨስትመንትን መሳብና በሌሎች የልማት ሥራዎች አበረታች ውጤት እንዲመጣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል። 

አክለውም የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሲቪል ሰርቪሱን ከብልሹ አሠራርና ከሙስና የጸዳ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ እስክንድር ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ የተተገበሩ አዳዲስ የሪፎርም ሥራዎች የሠራተኛውን ተነሳሽነት እንዳሳደጉ ተናግረዋል። 


 

የአገልግሎት አሰጣጥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተደረገው ጥረት በከተማዋ ዘርፈ ብዙ የልማት ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን አብራርተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ መሠረት ምትክ በበኩላቸው፤ በሥራ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍና አሠራርን በማሻሻል ሕብረተሰቡን በላቀ ደረጃ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

አክለውም የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ መሰል የመድረክ ውይይቶች አስፈላጊ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። 

አሠራሮችን በማሻሻል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተደረገው ጥረት ለሠራተኛው ተጨማሪ ተነሳሽነትን እንደፈጠረ የገለፁት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አሳምነው ወልደተንሳይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም