በክልሉ በቡሳ ጎኖፋ የመደጋገፍ እሴትን በማጎልበት ከተረጂነት የመውጣት ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በቡሳ ጎኖፋ የመደጋገፍ እሴትን በማጎልበት ከተረጂነት የመውጣት ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ ፤ነሃሴ 21/2018 (ኢዜአ) ፡-በክልሉ በቡሳ ጎኖፋ የመደጋገፍ እሴትን በማጎልበትና ምርታማነትን በማሳደግና ከተረጂነት የመውጣት ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ «ከተረጂነት ወደ አምራችነት» በሚል መሪ ሐሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በቡሳ ጎኖፋ የዳበረ እሴት የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት ከእርዳታ ጠባቂነት በማላቀቅ ሙሉ በሙሉ ራስን ለመቻል ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።
ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ዜጎችን መደገፍ ብቻ ሳይሆን እራሳቸውን ችለው ሕይወታቸውን መምራት እንዲችሉ በማድረግ ረገድ የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም አንስተዋል።
የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ በየና፤ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ከ29 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ አባላትን በማፍራት በተጠናከረ መልኩ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ መልሶ በማቋቋም ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም አክለዋል።
በክልሉ ባለፉት አራት አመታት 8 ሚሊዮን ኩንታል ለትምህርት ቤቶች ምገባ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በሻሸመኔ፣ አዳማ እና ጊኒር ከተሞች ዘመናዊ የእህል ማከማቻ መጋዘኖች በመገንባታቸውን ጠቅሰው በቀጣይ እስከ ወረዳ ድረስ የማስፋት እቅድ እንዳለም አንስተዋል።
በሀብት ማፍራት ረገድም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው አሁን ላይ በ13 ትራክተሮችና 8 ኮምፓይነሮች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሸገር ከተማ ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ወይዘሮ ወርቅነሽ ሚደቅሳ፤ በከተማዋ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ እና አባላትን በማፍራት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በተገኘው 100 ሚሊዮን ብር በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።