የቁልፍ መሰረተ ልማት የሳይበር ደኅንነት አዋጅን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የቁልፍ መሰረተ ልማት የሳይበር ደኅንነት አዋጅን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ የቁልፍ መሰረተ ልማት የሳይበር ደኅንነት አዋጅን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል የውይይት መድረክ መካሄዱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታወቀ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከቁልፍ መሰረተ ልማት አስተዳዳሪ ተቋማት ከተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት አዋጅ (ቁጥር 1426/2018) እና በሴክተር መለያ ስታንዳርድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ በወቅቱ አዋጁን ወደ ተጨባጭ ትግበራ ለማሸጋገር የመጀመሪያውና መሠረታዊው ተግባር በወጣው ስታንዳርድ መሠረት ቁልፍ መሰረተ ልማት ተቋማትን መለየትና መመደብ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገራችንን ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ከሳይበር ስጋቶችና ጥቃቶች መጠበቅ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ደኅንነት ከማረጋገጥ፣ ብሔራዊ ሉዓላዊነትን ከመጠበቅና ሀገራዊ ጽናትን ከመገንባት አንፃር ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ የአዋጁን አጠቃላይ ይዘት የሚያስተዋውቅ ገለጻ የቀረበ ሲሆን፣ አዋጁ ሀገራዊ የሳይበር ደኅንነትን ለማጠናከር፣ የጉዳት ስጋቶችን ለመቀነስ እና ለተቋማት ጥበቃ ግልጽ የሕግ ማዕቀፍ የሚዘረጋ መሆኑ ተብራርቷል።
በተጨማሪም "Critical Infrastructure and Sector Designation Standard" በሚል ርዕስ በቀረበው ገለጻ፣ ተቋማት በምን መስፈርት፣ ሂደትና የስጋት ግምገማ (Risk-based methodology) ቁልፍ ተብለው እንደሚለዩና ደረጃቸው እንደሚወሰን ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ስታንዳርዱ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ወሳኝነት፣ በስጋት ደረጃቸውና የሳይበር ጥቃት ቢደርስባቸው በሚያስከትሉት ሀገራዊ ተፅዕኖ ላይ ተመስርቶ ግልጽ አሰራርን የሚዘረጋ መሆኑ ተመልክቷል።
በውይይቱ ወቅት አዋጁንና ስታንዳርዱን በውጤታማነት ወደ መሬት ለማውረድ በኢመደአ እና በቁልፍ መሰረተ ልማት ተቋማት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ቅንጅታዊ አሰራር፣ የጋራ ኃላፊነትና የትብብር ማዕቀፍ ላይ ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም አዋጁ ሀገራዊ የሳይበር ጥበቃን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ገልጸው፣ ለትግበራው በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን የተቋሙ መረጃ አመላክቷል።