በክልሉ ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ሆነዋል
ጊዶሌ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸው ተገለጸ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በጋርዱላ ዞን ያስገነባው የአርጎባ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ተመርቋል።
በምረቃ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ ቦሼ ቦምቤ (ዶ/ር) እንደገለጹት በክልሉ በመደመር መንግሥት እሳቤ የተከናወኑ የልማት ተግባራት የህዝብን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው።
በተለይ የመስኖ አውታር መስፋፋቱ ወቅትን ጠብቆ ብቻ ግብርናን የማከናወን ባህልን ከመቀየር ባለፈ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ገቢን ለማሳደግ ማገዙን ጠቁመዋል።
የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ ሀብቶችን በመጠቀም አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ለማሳካት እየተሰራ ነው።
በዚህም በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የመስኖ ልማትን በማስፋፋት የአርሶና አርብቶ አደሮችን የምግብ ዋስትናና ገቢ ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱን ነው የገለጹት።
በጋርዱላ ዞን የተገነባው የአርጎባ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱ 180 ሄክታር መሬት በማልማት ከ800 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
የጋርዱላ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ግንኙነት ኪታሞ የመስኖ ፕሮጀክቱ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ዘላቂ ጠቀሜታ እንዲኖረውም ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግ ይሠራል ብለዋል።
በዞኑ የአርጎባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ንጉሤ ዳትኮ እና ካምባታ ካሊላ እንዳሉት፣ በአካባቢያቸው የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክት የዝናብ ወቅት ብቻ ጠብቀው ከማልማት እንዳሻገራቸው ተናግረዋል።
የመስኖ መሰረተ ልማቱን በሀላፊነት በመጠበቅ በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውንም አክለዋል።