ቀጥታ፡

በሰላም ማስከበር ዘርፍ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ከአካዳሚክ እውቀት ባለፈ ተግባራዊ ክህሎትንና የላቀ ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያገናዘቡ ናቸው -ሌተናል ጄኔራል ደሳለኝ ተሾመ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦በሰላም ማስከበር ዘርፍ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ከአካዳሚክ እውቀት ባለፈ ተግባራዊ ክህሎትንና የላቀ ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያገናዘቡ ናቸው ሲሉ የመከላከያ ኢንስፔክተር ጄኔራል ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደሳለኝ ተሾመ ገለጹ።

በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የጋራ ዓላማን አንግቦ መስራት ወሳኝ መሆኑንም የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ገልፀዋል።

የሰላም ማስከበር ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ከተለመደው ወታደራዊ ክህሎት ባለፈ የግጭቶችን ውስብስብ ባህሪ የሚረዱና ለውይይት ቅድሚያ የሚሰጡ ሙያተኞችን ማፈራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በሰላምና ግጭት አፈታት አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም የ3ኛ ዙር ተማሪዎቹን ዛሬ አስመርቋል።


 

የመከላከያ ኢንስፔክተር ጄኔራል ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደሳለኝ ተሾመ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የስልጠናው ዋና ዓላማ በሰላም ማስከበር ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን አቅምና ሙያዊ ብቃት ማሳደግ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ደረጃዎችና መልካም ተሞክሮዎች ጋር የሚጣጣም እውቀትና ክህሎት ማስታጠቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እና የተለያዩ ሀገራት ሠራዊት የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በብቃት መወጣት እንዲችሉ እያዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሰላምን፣ ውይይትንና የሰዎችን ክብር የሚያስቀድሙ መሪዎች እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ዘርፍ የካበተ ረጅም ጊዜ ልምድ እንዳላት ተናግረዋል።


 

ይህንን ልምድ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሰራር ጋር በማጣመር ብቁ ሰራዊት እየተገነባ ይገኛል ብለዋል። 

ማዕከሉ የሀገር ውስጥ አቅምን ከመገንባት ባለፈ ከአጋር ሀገራት ጋር አብሮ በመስራት ለአለም አቀፍ ሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት አዛዥ ኮሎኔል ጌቱ ታዬ፤ በመርሃ ግብሩ በበሰላም እና ግጭት አፈታት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁ ከኢትዮጵያና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 28 ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ትምህርቱ በመከላከያ ሚኒስቴር፣ በጃፓን መንግስትና በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ትብብር የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው የሴቶችና የውጭ ሀገራት ተማሪዎች መካተት ለፕሮግራሙ ትልቅ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።


 

ከተመራቂዎች መካከል ኮሎኔል ምትኩ ገመዳ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም የምታደርገውን አስተዋጽኦ አሁንም አጠናክራ እንደቀጠለች ጠቁመው ባገኙት እውቀት በተመደቡበት ማንኛውም ግጭት አፈታት ተልዕኮ ላይ ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ሌተናል ኮሎኔል ኤልሳቤት አዳነ በበኩላቸው፤ በትምህርታቸው በወታደራዊ ዲፕሎማሲና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ሰፊ እውቀት ማገኘታቸውንና ይህም በዓለም ደረጃ ያሉ የግጭት ሁኔታዎችንና የቅድመ-መከላከል ስልቶችን በግልጽ ለመረዳት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።


 

ያገኙት እውቀት በሚሰሩት ስራ ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብና በብቃት ለመስራት እንደሚያስችላቸው በመግለጽ በትግበራው ወቅት የተማሩትን ወደ ተግባር ለመቀየር መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ኮማንደር እፁብድንቅ መርሻ ናቸው።

ከውጭ ሀገር ሰልጣኞች መካከል ከዩጋንዳ የመጡት ዶክተር ደቪድ ኦኮሞ ሙኙዋ እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ ከተማሩባቸው በርካታ የዓለም ሀገራት ተቋማት መካከል ምርጡ እንደሆነ ገልጸዋል።


 

በአካልና በኦንላይን የተቃኘው የትምህርት አሰጣጥ ዘዴው በጣም ውጤታማና የተቀናጀ እንደነበር መስክረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም