የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከጋራ ተጠቃሚነትም ባለፈ ለቀጣናው ሰላም ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከጋራ ተጠቃሚነትም ባለፈ ለቀጣናው ሰላም ወሳኝ ነው
ጅማ፤ ነሐሴ 21/2018ዓም(ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከጋራ ተጠቃሚነትም ባለፈ የቀጣናውን ሰላም በአስተማማኝ መልኩ ለማስጠበቅ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
የአባይ መነሻ የሆነችውና ከቀይ ባህር በቅርብ እርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከሁለቱ ውሃዎች ጋር ህልውናዋ በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከጋራ የልማትና ተጠቃሚነትም ባለፈ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ወሳኝና አስፈላጊ ሀገር መሆኗ ይታመናል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሀ ምህንድስና መምህር እና ተመራማሪ ማሙዬ ቡሴር (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና መቀጠል የሌለባት በመሆኑ የባህር በር የግድ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።
ከባህር በር ባለቤትነቷም ባሻገር የቀይ ባህርን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የኢትዮጵያ አስፈላጊነት አማራጭ የሌለው መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከጋራ ተጠቃሚነትም ባለፈ ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
የቀጣናው አገራት በሁለቱ ውሃዎች ዙሪያ በትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው አንስተው ኢትዮጵያን ማእከል ያላደረገ ማንኛውም እንቅስቃሴ ውጤት ሊያመጣ አይችልም ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የኃይል ልማት ፍላጎት መሰረት አድርጎ የተገነባ ቢሆንም በተለይም የጎረቤት አገራትን የሃይል ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በቀይ ባህርም በተመሳሳይ መርህ በትብብር መስራት የግድ መሆኑን ያነሱት ተመራማሪው በተናጠል የሚደረጉ የልማትም ይሁን የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም ሲሉ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሃይድሮሊክስና የውሃ ሀብት ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህር ዋቅጅራ ታከለ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከራሷ ጥቅም ባለፈ ሌሎች አገራትንም ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የልማት ትስስርን ይዞ የሚመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የቀይ ባህር ጉዳይ በትብብርና በሰላማዊ የዲፕሎማሲ አማራጭ መምራት እንደሚገባ አንስተው በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው መርህ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ብርሀኑ ሞሲሳ (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በቅርበት፣ በመልካአ ምድርም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ አሳማኝና ተቀባይነት ያለው መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከጋራ ተጠቃሚነትም ባለፈ የባህር ላይ ወንጀሎችን ለመግታትና ሽብርተኝነትን ለመታገል የሚያስችል ቀጣናዊ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።
በሰላም ማስከበርና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና የሚታወቅ መሆኑን አንስተው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከጋራ ተጠቃሚነትም ባለፈ ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ ትልቅ አቅም የሚሆን ነው ብለዋል።