ቀጥታ፡

ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ልማትን ለማፋጠን የዜግነት ግዴታችንን እየተወጣን ነው- በድሬዳዋ ተሸላሚ ግብር ከፋዮች

ድሬዳዋ፣ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፡-ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ልማትን ለማፋጠን የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በድሬዳዋ ዕውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች ገለጹ።

የድሬዳዋ አስተዳደር በ2016 እና በ2017 ዓ.ም ግብራቸውን በታማኝነት ለከፈሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ዕውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።


 

ሽልማትና ዕውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የመንግስት ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ለድሬዳዋ ሁለንተናዊ ዕድገት የድርሻቸውን እየተወጡ ናቸው፡፡

አስተዳደሩም ለታማኝ ግብር ከፋዮች በየዓመቱ ዕውቅናና ሽልማት መስጠቱ ግብር ከፋዩ የዜግነት ሀላፊነቱን በታማኝነትና በወቅቱ እንዲወጣ ተነሳሽነት እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።

ከተሸላማዊቹ መካከል በሆቴል ሥራ የተሰማሩት ኤፍራታ ሚካኤል ግብራቸውን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈላቸው  የተሰጣቸው ዕውቅና እና ሽልማት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው።

የከፈሉት ግብር ለድሬዳዋም ሆነ ለሀገር እድገት ጠቀሜታ ስላለው የዜግነት ግዴታቸውን መወጣታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

ግብርን በታማኝነት ከፍሎ የዜግነት ግዴታን መወጣት ለአዕምሮ ሰላም የሚሰጥና ስራን በራስ መተማመን ለመፈፀም ያስችላል ያሉት ደግሞ ሌላው ተሸላሚ አቶ አስቻለው ብሩ ናቸው።

የንግዱ ማህበረሰብ ግብሩን በወቅቱና በታማኝነት መክፈሉ የድሬዳዋን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ለማፋጠን  ስለሚያግዝ ተግባሩን ማጠናከር እንዳለበት አስረድተዋል። 

ሌላው ተሸላሚ አቶ አሪፍ ጣሂር በበኩላቸው አስተዳደሩ የሰጣቸው የምስጉን ግብር ከፋይ ዕውቅናና ሽልማት የዜግነት ኃላፊነታቸውን ይበልጥ ለመወጣት እንዳነሳሳቸው አስታውቀዋል።

አስተዳደሩ ግብርን በቴክኖሎጂ መክፈል የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱ የግብር ከፋዩን እንግልት ከማስቀረት ባለፈ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ በማስቻሉ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በድሬዳዋ ለተመዘገቡ አበረታች የልማት ውጤቶች የታማኝ ግብር ከፋዮች ድርሻ የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው። 


 

በአስተዳደሩ የግብር አሰባሰቡን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ ዲጂታል አሰራርን ተደራሽ የማድረግ ሥራ መከናወኑንም  አስታውቀዋል።

አስተዳደሩ ታማኝ ግብር ከፋዮችን  ከማበረታታት ባለፈ በህገ ወጦች ላይ ተገቢውን እርምጃ የመወሰዱ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ለታማኝ ግብር ከፋዮች የተዘጋጁ ሽልማቶችን አበርክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም