የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በእርስ የመደጋገፍና ችግርን በጋራ የመፍታት ባህልን እያጎለበተ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በእርስ የመደጋገፍና ችግርን በጋራ የመፍታት ባህልን እያጎለበተ መጥቷል
ቦዲቲ ፤ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በእርስ የመደጋገፍና ችግርን በጋራ የመፍታት ባህልን እያጎለበተ መምጣቱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ አስተዳደር ለ10 የአቅመ ደካማ ቤተሰቦች የአብሮነት መንደር መኖሪያ ቤት ግንባታ ሥራን አስጀምረዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ለአቅመ ደካሞች ቤት በመገንባት፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ችግኝ በመትከልና መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን በማከናወን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ለማከናወን ወደ ተግባር መግባቱን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ የአብሮነት መንደር የመኖሪያ ቤት ግንባታ የማስጀመር ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት እርስ በርስ የመደጋገፍና ችግርን ተጋግዞ የመፍታት ባህልን እያዳበረ መጥቷል።
ሚኒስቴሩ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከላቸው ችግኞች አካባቢን በመጠበቅ ትውልድ ተሻጋሪ ጠቀሜታ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው በክልሉ የበጎነት ተግባር ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ህዝብን በማሳተፍና በማቀናጀት በተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች አቅም የሌላቸው በርካታ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የወላይታ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አማረ አቦታ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
በተያዘው ክረምት ብቻ 2 ሺህ 328 አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት እንዲሁም 2 ሺህ 73 ቤቶችን ለማደስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቦዲቲ ከተማ ከንቲባ አቶ ዘካሪያስ ጃታ በበኩላቸው ዛሬ በሚኒስቴሩ የግንባታ ሥራው የተጀመረው የአብሮነት መንደር በዜጎች መካከል እርስ በርስ መደጋገፍና ትስስርን ያጠናክራል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለግንባታው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ያሉት አቶ ዘካሪያስ፣ የአብሮነት መንደሩን ለሚያስገነቡ አካላት አመስግነዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሚኒስቴሩ፣ የክልሉ፣ የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።