ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ብቻ የመፍታት ባህልን ያጎለብታል

ሮቤ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ብቻ የመፍታት ባህል እንዲጎለብት ያደርጋል ሲሉ የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ለዘመናት በቆዩ ዘርፈ-ብዙ አለመግባባቶች ዙሪያ በመምከር በቀጣይ መሰል ውስብስብ ችግሮች እንዳይደገሙ ትልቅ የተግባርና የባህል ልምድ ጥሎ አልፏል። 

ከዚህም ዋነኛው የቱንም ያህል ጥልቅ እና ውስብስብ የሆኑ ሀገራዊ ቅሬታዎችና ልዩነቶች ቢኖሩ፣ ብቸኛውና ዘላቂው የመፍትሔ መንገድ የሐሳብ የበላይነትና በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ አካታች ውይይት ብቻ መሆኑን በተግባር ማረጋገጡ ነው። 

ሂደቱ ችግሮችን በኃይል ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ በመደማመጥ እንዲሁም የችግሮች አካል ከመሆን ይልቅ የመፍትሔው ባለቤት በመሆን መፍታት እንደሚቻል ትልቅ ትምህርትን የሰጠ ነው ።

በዚሁ ጉዳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለፁትም፤ የምክክር ጉባኤው ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ብቻ የመፍታት ባህልን ያጎለብታል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጫልቺሳ ዘውዴ፤ ጉባኤው ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል እንዲመክሩና እንዲወከሉ በማድረግ ሀገራዊ ስሜትን ያነቃቃ እንዲሁም ለችግሮች መፍትሔ እንዲገኝ በር የከፈተ ነው ብለዋል። 

"ምክክሩ ችግሮች ምንም ያህል ጥልቅ እና ውስብስብ ቢሆኑም፣ በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ ተቀምጦ መፍትሔ ማግኘት እንደሚቻል ያሳየ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ኢሳ ጣህር በበኩላቸው፤ ምክክሩ የቆዩ ቅሬታዎችን እና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ትልቅ ትምህርትን የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ሐጂ አሬሪ ሀሰን የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ በተለይ በታሪካችን ውስጥ የነበሩ ስብራቶችን ለማቃናት፣ ቅሬታዎችን ለመፍታትና የቆዩ ችግሮችን ለማስተካከል በውይይት የመፍታት ሰፊ ልምድን የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም